መስከረም 22 ቀን 2009 ዓ.ም.
ከአርበኞች ግንቦት 7
ዛሬ መስከረም 22 ቀን 2009 ዓም ዓመታዊ ባህላዊ የእሬቻ በዓል ለማክበር በሚሊዮን የሚገመት ሕዝብ ቢሾፍቱ (ደብረዘይት) ከተማ የሚገኝ ሀይቅ ዳር ተሰባስቦ ነበር። በበዓሉ ትውፊት መሠረት ለፈጣሪ ምሥጋና ለማቅረብ ብዙዎች ቄጠማ፣ ለምለም ሳርና አበባዎችን ይዘው ነበር። ሕዝቡ አጋጣሚውን በመጠቀም የህወሓት አገዛዝ በክልሉና በመላው ኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የሚያደሰውን በደል ለመቃወም የተቃውሞ ድምጾችን አሰማ፤ የተቃውሞ ምልክቶችን አሳየ።
ሕዝባዊ ተቃውሞ ባጋጠመው ጊዜ ሁሉ የሚሸበረው የህወሓት አገዛዝ ለሰላማዊ ተቃውሞ የሰጠው ምላሽ እንደተለመደው ጥይት ነበር። ሕዝብ በማንኛውም ቦታ ተቃውሞ የማቅረብ መብት አለው። በየትኛውም ዓለም ሕዝባዊ በዓላት ዓይነተኛ የተቃውሞ ማቅረቢያ ቦታዎች ናቸው። ተቃውሞው የቀረበበት ድባድ በጣም ሰላማዊየነበረ በመሆኑ የተለየ ጥበቃ ሊሰጠው ሲገባ የአገዛዙ ምላሽ ግን ከተለመደው የባሰ ሆነ። በታንኮች ላይ ከተጠመዱ መትረሶች ተኩሰው በርካታ ሰው መፍጀታቸው አልበቃ ሲላቸው በሄሊኮፕሮች ላይ በተጠመዱ መትረሶች ሕዝቡን ፈጁ። የሞተውና የቆሰው ሕዝብ ብዛት ምን ያህል እንደሆነ መናገር ለጊዜው አይቻልም፤ ያም ሆኖ ግን ሟቶች በመቶዎች ቁስለኞች ደግሞ በሺዎች ነው የሚቆጠሩት።
ዛሬ መስከረም 22 ቀን 2009 ዓም የአየር ኃይል፣ የፌደራልና የኦሮሚያ ክልል ፓሊስ ሠራዊትና የአጋዚ ክፍለ ጦር አባላት የፈፀሙት እጅግ አሳፋሪ ፋሽስታዊ ተግባር ለዘመናት የማይሽር ቁስል ፈጥሯል። “ነፃነታችንን እንፈልጋለን። የኦህዴድ ቅጥረኝነት ይብቃ፤ አማራን፣ ትግሬን፣ ጉራጌን፣ ኮንሶን፣ ... ኢትዮጵያውያንን በሞላ እንወዳለን! አንጣላላችሁም!" ማለታቸው ነው በጥይት ያስፈጃቸው። ይህ ዋጋ የሚያስከፍል ግፍ ነው። ዋጋ የሚስከፍል መሆኑ ደግሞ እያየን ነው፤ ሕዝባዊ እምቢተኝነቱ በመላው ኦሮሚያ እንደገና እየተቀሰቀሰ ነው። አሁን ኦሮሚያ ብቻውን አይደለም፤ የአማራ ወገኑ ከጎኑ አለለት፤ ኮንሶው፣ ሲዳማው፣ ጉራጌው፣ አፋሩ፣ ሶማሌው፣ ትግሬው ... የመላው ኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድነት ይነሳል። የቢሾፍቱው እልቂት የህወሓት መቀበሪያ ጉድጓድ ቁፋሮ ነው።
አርበኞች ግንቦት 7: የአንድነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ዛሬ መስከረም 22 ቀን 2009 ዓም በቢሾፍቱው እልቂት የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን ለሰማዕታቱ ቤተሰቦች እየገለፀ መጽናናትን ይመኛል፤ እንደዚሁም የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖቻችንም የተሰማውን ጥልቅ ስሜት ይገልፃል። አርበኞች ግንቦት 7 ከነገ ጀምሮ ያሉት ሶስት ተከታታይ ቀናት የሐዘን ቀናት እንዲሆኑ ያሳስባል።
ለሰማዕታትና ቁስለኛ ወገኖቻችን የሐዘን መግለጫዎችን መስጠት ችግሩን አይፈታውም፤ ይልቁንም የሞቱለትና የቆሰሉበት ዓላማ ከግብ ለማድረስ ጠንክረን መታገል ይኖርብናል። የህወሓት አገዛዝን በቢሾፍቱ በቆፈረው ጉድጓድ ውስጥ ለመቅበር ሁላችንም ተባብረን መነሳት የሚኖርብን ወቅት ላይ እንገኛለን።
ስለሆነም የተለየ ጥሪ ወይም የተለየ አመራር ሳትጠብቅ በሥርዓቱ የተማረርክ ሁሉ ከወዳጆችህ ጋር እየተቧደንክ ተነስ ! በየአካባቢው የሚገኘውን የአገዛዙን ወዋቅር እያፈረስክ የራስህን ጊዜዓዊ የሕዝብ አስተዳደር መስርት። አገራዊ ዓላማ ይኑርህ ትኩረት ግን በአካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ ይሁን። ሁሉም አካባቢውን ከህወሓት አገዛዝ ነፃ ያውጣ!
አንድነት ኃይል ነው !
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ !!!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ !!!
No comments:
Post a Comment