ኢሳት (ጥቅምት 21 ፥ 2009)
በኢትዮጵያ ተከስቶ ያለው የድርቅ አደጋ እኤአ እስከ 2017 አጋማሽ ድረስ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ድርጅት (UNOCHA) ዛሬ ሰኞ ባወጣው ሪፖርት አስታወቀ።
ድርቁ አርብቶ አደር በሆኑ በደቡብና በምስራቅ የአገሪቷ አካባቢዎች ማለትም በባሌ፣ ጉጂና፣ ቦረና ዞኖች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ታውቋል። ግጦሽ እና የውሃ አቅርቦት እየቀነሰ በመምጣቱ የቀንድ ከብቶች አካላቸው በተጎሳቆለ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ይኸው የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ድርጅት (UNOCHA) ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል።
በጉጂ እና በባሌ ዝቅተኛ ቦታዎች ችግሩ የከፋ መሆኑን ያስታወቀው ሪፖርቱ፣ የውሃ አቅርቦት ችግር እስከ መጋቢት ወር ድረስ ይቀጥላል ተብሎ እንደሚገመት ተገልጿል። በተመሳሳይ መልኩ በአፋር የተወሰኑ አካባቢዎች አሁንም ለችግሩ ተጋላጭ መሆናቸው የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ድርጅት (UNOCHA) በሪፖርቱ አስፍሯል።
ዝናብ በመዝነቡ ምክንያት በጥቂት አካባቢዎች የውሃ እጥረት የተቀረፈ ቢመስልም፣ በአብዛኞቹ የአፋር አካባቢዎች የውሃ እጥረቱ አሁንም ድረስ እጅግ ተባብሶ መቀጠሉ ታውቋል። በሶማሌ ክልል ደግሞ ባለፈው መስከረም መጣል የነበረበት ዝናብ ባለመዝነቡ ምክንያት በዶሎ አዶ ከፍተኛ የውሃ እጥረት እንደተከሰተ ሪፖርቱ ያብራራል።
ችግሩን ለመቅረፍ፣ በተለያዩ የደቡብና ደቡብ ምስራቅ አካባቢዎች በመኪና ቦቲዎች የውሃ አቅርቦት እየተካሄደ መሆኑ ተገልጿል።
የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ድርጅት (UNOCHA) እንዳለው፣ 2.9 ሚሊዮን ህጻናት ከትምህርታቸው እንዳይስተጓጎሉ የትምህርት መሳሪያዎች አቅርቦ ማድረጉንና ገልጾ፣ በዚሁ በያዝነው አመት 1.1 ሚሊዮን ለሚሆኑ ህጻናት ለምግብ አቅርቦት የሚሆን በጀት ይዞ ለተግባራዊነቱ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ ገልጿል።
No comments:
Post a Comment