Saturday, October 15, 2016

የአርበኞችግንቦት 7 ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ መግለጫ

የአርበኞች ግንቦት 7 ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ መደበኛ ስብሰባውን ከመስከረም 28 እስከ ጥቅምት 1 ቀን 2009 ዓ.ም. አካሂዶ በወቅቱ የአገራችን ሁኔታዎች ተነጋግሮ ውሳኔዎችን አሳልፏል፤ ሠራዊቱንም አነጋግሯል።


ሥራ አስፈፃሚው የአገራችን ፓለቲካዊ ሁኔታዎች በፍጥነት እየተለዋወጡ መሆኑና ተከታታይነት ያለው ወቅታዊና ውጤታማ አመራር መስጠት የሚገባ መሆኑ አጽንዖት ሰጥቶበታል። እንደ ሥራ አስፈፃሚው እምነት፣ በአገራችን የተለያዩ አካባቢዎች የተቀሰቀሰው ሕዝባዊ እምቢተኝነት በህወሓት የአገዛዝ ዘመን ደርሶ ወደማያውቅበት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል። ሕዝብ ለሚያቀርባቸ ጥያቄዎች ሁሉ ምላሹ ጥይት፣ እስርና ጉልበት የሆነው የህወሓት አገዛዝ በሚሰጣቸው ፋሽታዊ ምላሾች ሳቢያ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቻችንተሰውተዋል፤ በአስር ሺዎች የሚገመቱት ደግሞ ለእስር ተዳርገዋል። በዚህም ምክንያት ለውጥ ፈላጊው ሕዝብ ሕዝባዊ እምቢተኝነት ከሕዝባዊ አመጽ ጋር ለማቀናጀት ተገዷል፤ ሰላማዊ ዜጎች ራሳቸውን ለመከላከል መሣሪያ ለማንሳት ተገደዋል። ለፖለቲካ ችግሮች ፖለቲካዊ መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ ችግሩን በኃይል እወጣዋለሁ ብሎ እየሄደበት ያለው መንገድ ፈጽሞ እንዳይሳካ ማድረግና ይልቁንም ውድቀቱን የሚያፋጥን እንዲሆን ማድረግ የንቅናቄዓችን የጊዜው አብይ ተግባር መሆኑን ሥራ አስፈፃሚው አምኖበታል።ይህን እውን ለማድረግድርጅታችን የሕዝቡን ትግል በአግባቡ ማቀናጀትና መምራት ቀዳሚ ሥራው እንደሆነ የአርበኞች ግንቦት 7 ሥራ አስፈፃሚ ስምምነት ላይ ደርሷል።

በዚህም መሠረት ሥራ አስፈፃሚው በቀጣይ ወራት በሚከተሉት ጥቅል አቅጣጫዎች መነሻነት የተጠኑ ዝርዝር ተግባራትን ለማከናወን ውሳኔ አሳልፏል።

1ኛ) አገዛዙ ጭንቀቱን ለማስታገስ ያወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቀድሞውኑ ያልነበሩ መብቶችን የሚገፍ በመሆኑ ያመጣው አዲስ ነገር የሌለ ከመሆኑም ባሻገር የመቀበሪያ ጉድጓዱን በጥልቁ እየቆፈረ እንደሆነ ሕዝብን ማስረዳት፤

2ኛ) ሕዝባዊ እምቢተኝነት እስካሁኑ ከነበረው ተጠናክሮ እንዲቀጥልና መላዋን ኢትዮጵያ እንዲያዳርስ ጠንክሮ መሥራት፤ በተለያዩ አካባቢዎች የሚደረጉ የሕዝባዊ እምቢተኝነት ተግባራትን በተመሳሳይ ጊዜ እንዲደረጉ ማቀናጀት፤

3ኛ) በተለይ በአማራ ክልል በግልጽ እንደታየው ሕዝብ ራሱን የሚከላከልበት አደረጃጀት መኖር እንደሚገባ በመገንዘብ በየቦታው ሕዝባዊ እምቢተኝነትና አዝባዊ አመጽ ተደጋግፈው የሚሄዱበት መንገድ ማመቻቸት፤ ሕዝብን ከጥቃት የሚከላከሉ ቡድኖችን ማደራጀት፣ ማሰልጠንና አቅማቸውን ማጎልበት፤ በሕዝቡ የራስ መከላከል ትግል ውስጥ ቀጥተኛ ተሳትፎ ማድረግ፤

4ኛ) ሕዝብ ለነፃነቱና ለመብቶቹ መከበር የሚያደርገውን ትግል ወደ ዘርና ሃይማኖቶች ግጭት እንዲያመራ የህወሓት አገዛዝ የሚያደርገውን ስውርና ግልጽ ጥረቶችን ተከታትሎ ማክሸፍ፤

5ኛ) የአገዛዙ የጦርና የፓሊስ ሠራዊት አባላት ሥርዓቱን ከድተው የሕዝብን ትግል እንዲቀላቀሉ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ፤

6ኛ) በሲቪል የመንግሥት ሥራ ላይ ያሉ ወገኖቻችን በሥራቸው ላይ እንዳሉ ሥርዓቱን የሚያዳክሙ ተግባራትን እንዲሠሩ ማበረታታት፤

7ኛ) በብአዴን፣ ኦህዴድ፣ ደህዴድ እና በራሱ በህወሓት ውስጥ እንዲሁም በአጋር ድርጅቶች ውስጥ የሚገኙ ህሊና ያላቸው ወገኖች ድርጅቶቹን ለቀው እንዲወጡ፤ አለበለዚያ ድርጅቶቻቸውንከውስጥ ሆነው እንዲያፈርሱ መሥራት፤

8ኛ) ሲቪክ ማኅበራትና የሃይማኖት ተቋማት ለሰብዓዊ መብቶች መከበር እንዲቆሙ ማበረታታትና ማገዝ፤

9ኛ) አርሶ አደሮች፣ ሠራተኞች፣ ተማሪዎች፣ መምህራን፣ ነጋዴዎች እና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በኢትዮጵያ ውስጥ የፓለቲካ ሥርዓት ለውጥ እንዲመጣበተደራጀ መንገድ እንዲታገሉ አመራር መስጠት፤

10ኛ) ተመሳሳይ ዓላማዎችካለን ድርጅቶች ጋር ትብብሮችን መመሥረትና በጋራ መታገል፤

11ኛ) ከህወሓት አገዛዝ መውደቅ በኋላ የሚመጣው የፓለቲካ ሥርዓት ፍትህ፣ ነፃነት፣ እኩልነትና የአገር አንድነት የተከበረበት እንዲሆን ዋስትና የሚሰጥ የሽግግር ወቅት ምን መምሰል እንደሚኖርበት ካሁኑ ማሰብና መዘጋጀት፤ እና

12ኛ) የህወሓት አገዛዝ በሕዝብ የተጠላ እና ከእንግዲህ ለአንድ ቀን እንኳ የሚያቆይ ተቀባይነት የሌለው ህገወጥ አገዛዝ መሆኑን ለዓለም ኅብረተሰብ ለማሳወቅ ጠንካራ የዲፕሎማሲና አድቮኬሲ ሥራዎችን መሥራት፤

እነኝህን ሥራዎች ከሕዝባችን ጋር ሆነን በአስቸኳይነት ስሜት በመሥራት የህወሓት/ኢህአዴግን አገዛዝ እድሜ እንደምናሳጥር ቅንጣት ታህል ጥርጥር የለንም።

አንድነት ኃይል ነው !
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ !!!`

No comments:

Post a Comment