Monday, October 3, 2016

በቢሾፍቱ ከተማ በእሬቻ በዓል ላይ የሞቱ ተጨማሪ አስከሬኖች መገኘታቸው ተገለጸ

ኢሳት (መስከረም 23: 2009)
በቢሾፍቱ ከተማ ዕሁድ ከእሬቻ በዓል አከባበር ጋር በተገናኘ የሞቱ ሰዎች ተጨማሪ አስከሬን ሰኞ ጠዋት መገኘቱን እማኞች ለኢሳት ገለጹ። 
የቤተሰብ አባሎቻቸውን ያጡ በርካታ ሰዎች በሆራ ሃይቅ ዙሪያ በመሰባሰብ በሞት የተለዩ ሰዎችን በመፈለግ ላይ ሲሆኑ በትንሹ የ10 ሰዎች አስከሬን ከ24 ሰዓት በኋላ መገኘቱን የከተማዋ ነዋሪዎች አስታውቀዋል። 
የቢሾፍቱ ከተማ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ አቶ ደሳለኝ ባይሳ በበኩላቸው፣ አደጋው በደረሰ ማግስት ሰኞ ጠዋት ብቻ ሆስፒታሉ የአንድ ሰው አስከሬን መረከቡን ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል። 
ይሁንና የከተማዋ ነዋሪዎችና እማኞች በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የገቡበት ያልታወቁ ሰዎችን ለማፈላለግ አሁንም ድረስ በበዓሉ አከባበር ስፍራ በለቅሶ እና በሃዘን ውስጥ መሆናቸውን አስረድተዋል። 


የበዓሉ ስነ-ስርዓት በሚካሄድበት ስፍራ ለበዓሉ አከባበር ሲባል ተቆፍሯል በተባለ ጉድጓድ ውስጥ በርካታ ሰዎች መሞታቸው የሚታወስ ሲሆን፣ በሆራ ሃይቅ ውስጥም የሞቱ ሰዎች እንደሚኖሩ ተነግሯል።
የቤተሰብ አባሎቻቸውን ያጡ ስዎች በሃይቁ ዙሪያ ሰፍረው የሚገኙ ሲሆን፣ ዋናተኞች በሃይቁ ውስጥ አስከሬን ሊገኝ ይችላል በሚል ፈለጋ በማካሄድ ላይ መሆናቸውንም መረዳት ተችሏል።
በሬቻ በዓል አከባበር ወቅት በርካታ ሰዎች በቅርቡ በክልሉ የተገደሉ ሰዎችን ድርጊት በማወግዝ ተቃውሞ በማሰማት መጀመራቸው የሚታወስ ሲሆን፣ የጸጥታ ሃይሎች የወሰዱት የተኩስ እርምጃ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ሞት ምክንያት መሆኑን ተነግሯል።
የመንግስት ባለስልጣናት የጥይት ተኩስ እንዳልተወሰደ ቢያስተብሉም በበዓሉ የታደሙ ሰዎች እንዲሁም የቪዲዮ ፊልሞች የጥይትና አስለቃሽ ጢስ ጥቅም ላይ መዋሉን አረጋግጠዋል።
የሶሼይትድ ፕሬስ፣ ቢቢሲ እና የተለያዩ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ተቃውሞውን ለመቆጣጠር የወሰዱት ድርጊት ለበርካታ ሰዎች ሞት ምክንያት መሆኑን በመዘገብ ላይ ናቸው።
የተለያዩ አካላት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መሞታቸውን ቢገልጹም፣ መንግስት ጠዋት ድረስ የሟቾች ቁትር ከ52 ወደ 55 መድረሱን ገልጿል።

No comments:

Post a Comment