Sunday, June 7, 2015

ወያኔ የጋረደብንን የመበታተን አደጋ ለማክሸፍ ትግላችንን ማቀናጀትና በአንድ የአመራር ጥላ ሥር ማሰባሰብ ወቅቱ የሚጠይቀን እርምጃ ነው

ትግራይን ከተቀረው የአገራችን ክፍል ለመገንጠልና የትግራይን ሪፑፕልክ ለማቋቋም ራዕይና ተልዕኮ ሰንቆ የዛሬ 40 አመት ደደቢት በረሃ ውስጥ የተፈጠረው ህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ፡ በለስ ቀንቶት የመንግሥት ሥልጣን ከተቆጣጠረ ወዲህ፡ በስሙ የሚነግድበትን የትግራይን ህዝብ ጨምሮ በአገራችንና በመላው ህዝባችን ላይ የፈጸማቸው ወንጀሎችና ያደረሳቸው ሰቆቃዎች ተዘርዝረው የሚያልቁ አይደሉም::

ከነዚህ ወንጀሎች ሁሉ የከፋውና ምናልባትም የሚቀጥለውን ትውልድ ጭምር ዋጋ ያስከፍላል ተብሎ የሚፈራው ምዕራባዊያን ቅኝ ገዥዎች አህጉራችን አፍሪካን በተቀራመቱበት ወቅት የአገዛዝ ዘመናቸውን ለማራዘምና ቅኝ የገዙዋቸውን ህዝቦች ሃብትና ንብረት ለመዝረፍ እንዲመቻቸው የተጠቀሙበትን የከፋፍለህ ግዛ ፖሊስ በምድራችን ተግባራዊ በማድረግ ለዘመናት የተገነባውን የህዝብ አንድነትና የአገር ሉአላዊነት ሊያናጋ በሚችል መልኩ በዘር፤ በቋንቋና በሃይማኖት ተከፋፍለን የጎሪጥ እንድንተያይ የተፈጸመብን ደባ ነው::



በዚህ ደባ ምክንያት ዛሬ በአገራችን ታሪክ ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ ሆኔታ ኦሮሞነት፤ ሱማሌነት፤ ትግሬነት፤ አማራነት ፤ ስዳማነት፤ አፋርነት፤ ወላይታነት ፤ ከምባታነት ወዘተ ከዘግነት በላይ ገዝፎ የማንነት መለያና የፖለቲካ፤ የኢኮኖሚና ማህበራዊ መብቶች መሠረት ሆኖአል:: በዚህም የተነሳ የኦሮሞ ከብት አርቢ ለከብቶቹ ግጦሽ ፍለጋ ወደ ሱማሌ ድንበር ከተሻገረ እንደ ባዕድ ተቆጥሮ ተኩስ ይከፈትበታል፤ አፋር ወደ ኢሳ ከተሻገረ ይገደላል፤ ለቤነሻንጉል በተከለለ ክልል የሰፈረ የአማራ አርሶ አደር የደከመበትን አንጡራ ሃብት ተቀምቶ ይባረራል፤ አኝዋክ ለዘመናት ተከባብሮና ተቻችሎ ከኖረው ከኑዌር ወንድሙ ጋር እንዲጋጭ ተደርጎ በገላጋይነት ሥም የፈደራል ፖልስና የጸጥታ ሃይል በጅምላ እንዲጨፈጭፈው ይፈረድበታል :: በመልካም አስተዳደር እጦት የደረሰበትን መከራና ስቃይ አብሮ ሲጋፈጥ የኖረው የወልቃይት ጠገደ ህዝብ አንተ አማራ አንተ ትግሬ በሚል የዘር ክፍፍል ለመገዳደል ካራውን ስሎ ተቀምጦአል :: ይህ አልበቃ ብሎም የአንድ ብሄር አባላትን በጎሳ ሸንሽኖ የጉጂ ኦሮሞ ከአርስ ወንድሙ ጋር ደም እንዲቃባ ተደርጎአል:: የኦጋዴን የተለያዩ ጎሳዎችም ላይ እንዲሁ::

ወያኔ በጉልበት የጫነብን የመከፋፈልና የመለያየት አደጋ አንድ ቀን ሲያበቃ የነጻነት ብርሃን ፈንጥቆ በሠላምና በመቻቻል የምንኖርበት አገር እንኳ እንዳይኖረን በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች መጠነ ሰፊ የሆነ ድንግል መሬታችንን ለህንድ፤ ለቻይናና ለአረብ ከበርቴዎች በርካሽ ዋጋ በመቸብቸብ በገዛ አገራችን የባዕዳን አሽከሮች ሆነን እስከ ዘለአለሙ እንድንኖር መሠረት ተጥሎአል::

ይህ ሁሉ በደልና መከራ እንዲያበቃ በአገዛዙ ላይ የተቃውሞ ድምጹን ያሰማ ከሥራውና ከኑሮው ተፈናቅሎ በድህነት አረንቋ ውስጥ እንዲጣል አለያም እየታደነና የሽብርተኝነት ታፔላ እየተለጠፈበት ወደ የማጎሪያ ጥቢያዎች እንዲወረወር ተደርጎአል:: በዘርና በቋንቋ በተከለለልን ክልል በፈረቃ የሚደርስብንን አፈናና ሰቆቃ በህብረት ለመቃወም የሚደረጉ ጥረቶች በሙሉ “የቀድሞ ሥርዓት ናፋቂ፤ ትምክህተኛ ፤ አክራሪ/ጽንፈኛ፤ ጸረ ልማት ወዘተ ” በሚሉ የማሸማቀቂያና የመወንጀያ ቃላቶች ጋጋታ እንዲደናቀፍ ለማድረግ ተሞክሮአል::

ግንቦት 7 የፍትህ የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄና የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር ጥር 2 ቀን 2007 አመተ ምህረት የፈጸሙት ውህደት ዋናው ምክንያት ከላይ የተዘረዘሩትን ግፎች ለማስቆም በተናጠል ከሚደረግ ትግል በህብረት የሚደረገው ትግል ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ መሆኑ የፈጠረው ግንዛቤ ነው :: የወያኔ የጥቃት ክንዶች የፈረጠሙት በራሱ ጥንካሬ ወይም የሚተማመንበት ህዝባዊ ድጋፍ በደጀንነት ኖሮት ሳይሆን በኛ መከፋፈልና መለያየት ብቻ እንደሆነ ህዝባችን ከተረዳው ውሎ አድሮአል::

አርበኞች ግንቦት 7 በሚል መጠሪያ ሁለቱ ድርጅቶች በቅርቡ የፈጠሩት ውህደት ከድህረ ምርጫ 97 ጀምሮ ህዝባችን ከደረሰበት ስቆቃ ለመገላገል ተቃዋሚዎችን “ተባበሩ ወይም ተሰባበሩ” በማለት ሲያቀርብ ለኖረው የድረሱልኝ ጥሪ የተሰጠ የመጀመሪያው ተግባራዊ ምላሽ ነው:: ሁለቱም ድርጅቶች እስከ ዛሬ ምድር ላይ ያደራጁትን የሰው ሃይል ፤ እውቀትና ንብረት አዋህደው በአንድ አመራር ሥር ትግሉን ከዳር ለማድረስ መወሰናቸው በአላማና ግብ ለሚመሰሉዋቸው ሌሎች ተቃዋሚ ሃይሎች ብቻ ሳይሆን ወያኔን ከህዝብ ጫንቃ ላይ በማውረድ ፍትህና እኩልነት በአገራችን እንዲሰፍን እንታገላለን ለሚሉት ሃይሎች ሁሉ አርአያነት ያለው እርምጃ መሆኑ እየተነገረ ነው :: የአርበኞች ግንቦት 7 ውህደት በተፈጸመበት ሥነሥርዓት ላይ አገራቸውን ነጻ ለማውጣት ነፍጥ አንግበው ከሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ውስጥ የትግራይ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ [ዴሚት] ሊቀመንበር አቶ ሞላ አስግዶም ፡ የአፋር ነጻነት ግንባር [አርዱፍ] ሊቀመንበር አቶ ኢብራሂም ሙሳ ፤የጋምቤላ ህዝብ ነጻነት ንቅናቄ [ጋህነን] ሊቀመንበር አቶ ኦኬሎ አይዴድ ፡ የቤነሻንጉል ተወካይና የአድሃን ተወካዮች በየተራ የተናገሩት በአንድ የጋራ ግንባር ሥር ተሰባስቦ በገንዘብና በመሣሪያ ብዛት ተብቶ የህዝባችንን መከራና ስቃይ እድሜ እያራዘመ ያለውን የጥቂቶች አገዛዝ በሃይል የማንበርከክ አስፈላግነትና ወቅታዊነት ሁለቱ ድርጅቶች የፈጸሙት ውህደት ለትብብር ፈር ቀዳጅ መሆኑን አመላክቶአል :: አገራችንን ከመበታተን አደጋ ለመታደግ ወያኔ ባወጣቸው የአፈና ህጎች ተገዝተን ለውጥ ማምጣት አንችልም ያልን ሃይሎች እየተዋሃድንና እየተጣመርን በሄዱን ቁጥር አፈናና እንግልት ተቋቁመን እንታገላለን ያሉት ሃይሎችም በተናጠል ከሚደርስባቸው ጥቃት ለመገላገል ሲሉ ወደ ውህደትና ጥምረት ጎዳና ማቅናታቸው የማይቀር ነው::

ህዝባችን ላይ የደረሰው ግፍና መከራ ጻዋ ሞልቶ እየፈሰሰ ባለበት በዚህን ሰዓት የአገሩ ጉዳይ አሳስቦት በፖለቲካ ድርጅቶች ዙሪያ የተሰባሰበ ወገን ሁሉ ለመቀራረብና ለመተባበር እያደረገ ያለው ጥረት ተስፋ ሰጪና አበረታች ሆኖአል:: በዚህ አጋጣሚ ላለፉት 24 አመታት ወያኔ በወገኖቻችን ላይ ለፈጸማቸው ሰቆቃዎች በመሣሪያነት ያገለገሉና እያገለገሉ ያሉ ወገኖች በሙሉ ከውህዱ አርበኞች ግንቦት 7 የአንድነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ አንድ የተላለፈላቸው ወገናዊ ጥሪ አለ:: ይህም ጥሪ እስከ ዛሬ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ወይም ለሥራ ዋስትና ብላችሁ የዚህ ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ መሳሪያ በመሆን በወገኖቻችሁ ላይ ግዲያ ፤ እስርና ግርፋት ስትፈጽሙ የኖራችሁ ሁሉ የበደላችሁትን ህዝብ ለመካስ የአገዛዙን ዕድሜ ለማሳጠር በምናደርገው የሞት ሽረት ትግል ላይ እንቅፋት ከመሆን እራሳችሁን አግልሉ ! የሚል ነው:: ትግላችን ወሳኝ የታሪክ ምዕራፍ ላይ ገና ከመድረሱ ከህዝብ በዘረፉት ሃብትና ገንዘብ ልጆቻቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ወደ ባህር ማዶ ማሸሽ ለጀመሩት ስግብግብ አለቆችህ ምቾትና ድሎት ብለህ ይህ የመከራ ዘመን ሲያልፍ በሃላፊነት የሚያስጠይቅህን ወንጀል ለነጻነት በሚታገሉ ወገኖችህ ላይ እንዳትፈጽም ለአገር የመከላኪያ ሠራዊት፤ ለፖልስና የጸጥታ ሃይል አባላት ሁሉ ጥሪ ቀርቦአል::

የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በቀር ድል ማድረጋችንን ፈጽሞ የማንጠራጠር የነጻነት ታጋዮች በሙሉልብ የምንናገረው ወያኔ አገራችንን ለመበታተን የቻለውን ሁሉ ድንጋይ ቢፈነቅልም በአንድ የአመራር ጥላ ሥር ተሰባስበን አገራችንን ከተጋረጠባት የመበታተን አደጋ ለመታደግና እያንዳንዱ ዜጋ የሚኮራባት የበለጸገችና ሉአላዊነቷ የተረጋገጠ አገር ባለቤት ለመሆን የጀመርነው ትግል ግቡን እንደሚመታ ነው:: ለዚህ ደግሞ በቅርቡ የፈጸምነው ውህደትና ከሌሎች ጋር በጥምረት ጠላትን ለመፋለም የጀመርነው ተግባራዊ እንቅስቃሴ ወቅታዊነት ለወገን ተስፋ ለጠላት መርዶ ነው::

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !


No comments:

Post a Comment