Sunday, June 28, 2015

በወጣት ተመስገን ላይ እየተፈጸመ ያለው በደል የኢህአዴግ የግፍ አስተዳደር መገለጫ ነው ሲል መድረክ አስታወቀ

ሰኔ ፲፱ (አስራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ወጣት ተመስገን ታፈሰ ተሰማ ዕድሜው 22 ዓመት ሲሆን በትምህርት ደረጃውም በማኔጅመንት የመጀመሪያ ድግሪ ያገኘ ወጣት ነው፡፡ ትውልዱና ዕድገቱ በደቡብ ክልላዊ መንግስት በቡርጂ ወረዳ ውስጥ ሲሆን በአሁኑ ወቅት የኢማዴ-ደህአፓ/መድረክ አባል ሆኖ ለመታገል የወሰነና በመድረክ አባልነታቸው ምክንያት በሀገራቸው ሠርተው የመኖር የዜግነት መብታቸውን እየተነፈጉ አስተዳደራዊ ግፍ እየተፈጸመባቸው ካሉ ወጣቶች አንዱና ተጫባጭ ምሳሌ ሆኖ የሚገኝ ወጣት ነው ብሎአል መድረክ።
መድረክ የወጣቱን በደል ሲዘረዝር “የቡርጂ ወረዳ መንገድ ትራንስፖርት ጽ/ቤት ለትራንስፖርት አቅርቦት አደረጃጀት ስምሪት ባለሙያ፣ የሥራ መደብ ሠራተኛ ለመቅጠር በ05/09/07 የቅጥር ማስታወቂያ አወጣ፡፡ በማስታወቂያው መሠረት የጽሑፍና የቃል ፈተናዎች የተሰጡ ሲሆን የጽሑፍ ፈተናው ከመቶ ዘጠና፣ የቃል ፈተናው ከመቶ አምስት እና የትምህርት ማስረጃው ከመቶ አምስት እንዲይዝ ተደርጎ ውድድሩ ተካሄደ፡፡ ይኼው ጽ/ቤት በ18/09/07 በቁጥር 327-ኢ2-05 ባወጣው የውድድር ውጤት መግለጫ ማስታወቂያ መሠረት አቶ ተመስገን በጽሑፍ ፈተናው 84፣ በቃል ፈተናው 5፣ እና በትምህርት ማስረጃው 5 በድምሩ 94 ከመቶ በመግኘት በከፍተኛ ነጥብ አንደኛ ወጥቶ አለፈ፡፡ ” ይላል።

መድረክ በመቀጠልም ” በ19/09/07 ልክ ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት ላይ ለጽ/ቤቱ ሪፖርት እንዲያደርግም በማስታወቂያው ተገልጾለት፣ ወጣቱም በተገለጸለት መሠረት ሪፖርት አደረገ፡፡ ጽ/ቤቱም በዕለቱ ወጣቱ የጤናና የጣት አሻራ ምርመራ ውጤቶችን እንዲያቀርብ ለቡርጂ ወረዳ ጤና አጠባበቅ ጣቢያ እና ለወረዳው ፖሊስ ጽ/ቤት በቁጥር 328/አ-1/ሠ14/07 እና 329/አ-1/ሠ14/07 የትብብር ደብዳቤ ጽፎ ለወጣቱ ሰጠ፡፡ የቡርጂ ወረዳ ፖሊስ ጽ/ቤት ለጌዴዎ ዞን ፖሊስ መምሪያ የጣት አሻራ ምርመራ ተደርጎ ውጤቱ እንዲቀርብ ደብዳቤ የጻፈ ሲሆን የዞኑ ፖሊስ መምሪያና የቡርጂ ወረዳ ጤና ጣቢያም ከወንጀል ነፃ የጣት አሻራና ሙሉ ጤናማነቱን የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች ሰጥተውት እነዚሁኑ ማስረጃዎች ወጣቱ ለቀጣሪው ጽ/ቤት አቅርቦአል፡፡” ብሎአል።
ወጣት ተመስገን ከላይ በተራ ቁጥር 5 የተጠቀሱ ማስረጃዎችን ለጽ/ቤቱ ለማቅረብ ሲንቀሳቀስ በነበረበት ወቅት ፣ወጣቱ የመድረክ አባል መሆኑና በ16/09/07 በሀገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደው ምርጫ በወረዳው ውስጥ በሚገኝ ደኬ በተባለ ምርጫ ክልል የመድረክ ታዛቢ/ወኪል ሆኖ መሥራቱ በወረዳው የኢህአዴግ ባለሥልጣናትና በቀጣሪዎቹ በመታወቁ፣ ወጣቱ ማስረጃዎቹን ይዞ በቀረበበት ዕለት ፣ ጽ/ቤቱ የበጀት እጥረትን በማሳበብ በ21/09/07 የተጻፈ የሥራ መደቡ የቅጥር ስረዛ ማስታወቂያ አወጣ። የጽ/ቤቱ ኃላፊ አቶ እሥራኤል ገብረ በጽ/ቤቱ በር ላይ አገኝተውት የመድረክ አባልነቱንና የምርጫ ታዛቢነቱን እንደበጥባጭነት ቆጥረው ” ለካ አንተ ሀገር በጥባጭ ነህ፣ ደርሰንብሃል” በማለት በምስጉን ፀባዩና በታታሪ ተማሪነቱ በአካባቢው ሕብረተሰብና በተማረባቸው ትምህርት ቤቶች መምህራንና ተማሪዎች የሚታወቀውን ተመስገንን በመሳደብ ሊቀጠር እንደማይችል ፎክሮበታል” ብሎአል።
ከዞኑ ሲቭል ሰርቪስ ጽ/ቤት ድርጊቱ ሕገወጥ ስለሆነ በወጣቱ ላይ የተፈጸመው በደል እንዲታረም ደብዳቤ ለወረዳው የተጻፈ ቢሆንም የወረዳው ባለስልጣናት በሥራው ላይ ሊመድቡት ፈቃደኞች ሆነው አልተገኙም የሚለው መድረክ፣ ስለሆነም ወጣቱ በወረዳውም ሆነ በዞን ደረጃ ላሉትና ጉዳዩ ለሚመለከታቸው መሥሪያ ቤቶች እየተመላለሰ ላቀረባቸው አቤታዎች እልባት ስላልተሰጠ በከፍተኛ ደረጃ እየተጉላላ ይገኛል ብሎአል።
በአሁኑ ወቅት በብዙ አከባቢዎች በርካታ የኢህአዴግ ባለሥልጣናት በዚህ አይነቱ ፖለቲካዊ ወገንተኝነት በሰፈነበት ብልሹ አስተዳደራቸው እንደተመስገን ታፈሰ ያሉ በርካታ ብርቅዬ ወጣቶቻችንን በሀገራቸው ሠርተው የመኖር መብታቸውን እየገፈፉ “ለአስከፊ ስደት፣ በሰው ሀገር ለስቃይና ለእንግልት እንዲሁም ለአሰቃቂ ሞት እንዲዳረጉ በማድረግ ላይ ናቸው ሲል መድረክ ወቅሷል።
“ይህ አይነቱ ጭፍን አምባገነናዊ እርምጃቸው ግን የሀገራችን ወጣቶች እነርሱ እንደተመኙት እንዲንበረከኩላቸው የሚያደርግ ሳይሆን በይበልጥ የግፍ አገዛዛቸውን እንዲረዱና ከዚሁ የግፍ አገዛዛቸው ነፃ ለመውጣትና ሕገመንግሥታዊ የዜግነት መብታቸውን በተግባር ለማረጋገጥ በቆራጥነት ለትግል እንዲነሱ እንደሚያደርጋቸው የሚያጠራጥር አይደለም” ሲል መድረክ መግለጫውን አጣቃሏል።


No comments:

Post a Comment