Wednesday, June 24, 2015

አንድ ኢህአዴግን ከድተዋል የተባሉ ጎልማሳ በኢትዮጵያ የደህንነት ሃይሎች ሰሃራ በረሃ አቅራቢያ ተገደሉ፣ ሌሎች አምስት ወጣቶችም በአደጋው አልቀዋል

ሰኔ ፲፯ (አስራ ሰባት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ያሬድ ንጉሴ የተባለ ባለፈው ወር አውሮፓ የገባ አንድ ኢትዮጵያዊ ስደተኛ ለኢሳት እንደገለጸው በቅርቡ 25 ኢትዮጵያውያንና 2 ኤርትራውያን ሆነው ከሱዳን ወደ ሊቢያ ሲጓዙ፣ ደንጎላ በምትባል ቦታ ላይ በሱዳን የመከላከያ ሰራዊት አጃቢነት የመጣ ኢትዮጵያዊ የደህንነት ሰራተኛ የ48 አመት ጎልማሳ የሆነውን ኢትዮጵያዊ ግለሰብ ከመኪና አስወርዶ በሽጉጥ እንደገደለው ገልጿል። “ወታደሮችን የጫነው መኪና” ከጎን በኩል መጥቶ የተሳፈርንባትን መኪና ሲጋጫት ሁላችንም ወደ ጎን ወደቅን የሚለው ያሬድ፣ ሁለት ወጣት ባለትዳሮችን ጨምሮ 5 ወጣቶች ወደያውኑ ሞታቸውን በፎቶአስደግፎ ተናግሯል።
የልጆቻቸውን መሞት ላልሰሙት ወላጆች ሲባል ኢሳት በአደጋው የሞቱትን ኢትዮጵያውያን ስም ይፋ ከማድረግ ተቆጥቧል። እንዲሁም መሞታቸው የተነገረው የቀድሞው የኢህአዴግ አባል ስምም ለቤተሰቦቻቸው ሲባል ይፋ አያደርግም።
ሟቹ የቀድሞው የኢህአዴግ አባል ” እግዚአብሄር በሰላም ያስገባኝ እያሉ” ሲጸልዩ እንደበር የሚናገረው ያሬድ፣ የደህንነት ሰራተኛው ፎቷቸውን ይዞ ከመጣ በሁዋላ ከመኪና ላይ አውርዶ በሽጉጥ ገድሏቸዋል ብሎአል። የደህንነት ሰራተኛው መገናኛ ሬዲዮ ይዞ እንደነበርም ተናግሯል።
የ5ቱ ኢትዮጵያውያንን አስከሬን ሰሃራ በረሃ ላይ ቀብረው በአካባቢው ነዋሪዎች ድጋፍ ተርፈው በመጨረሻ ሊቢያ መግባታቸውንም ገልጿል።
ኢትዮጵያውያንን ከሱዳን ወደ ሊቢያ እንዲሁም ወደ አውሮፓ በማሻገር በኩል ሱዳን የሚገኘው ኢምባሲ ሰራተኞች እጅ እንዳለበት ያሬድ ተናግሯል። በተዘዋዋሪ መንገድ ገንዘብ የምንሰጠው ለኢምባሲ ሰራተኞች ነው የሚለው ያሬድ፣ የግለሰቦችን ስም እየጠቀሰ የተዘረጋው መረብ ምን እንደሚመስል አጋልጧል። ከያሬድ ንጉሴ ጋር የተደረገው ቃለምልልስ ሰሞኑን ይቀርባል። በጉዳዩ ዙሪያ ሱዳን የሚገኘውን የኢትዮጵያን ኢምባሲ ለማነጋገር ሙከራ ብናደርግም አልተሳካልንም


No comments:

Post a Comment