Friday, June 12, 2015

የሱዳን ጦር የኢትዮጵያ ድንበር በመጣስ ጥቃት ፈጸመ!፡፡ 

ኢሳት ዜና (ሰኔ 4 2007)

የሱዳን መከላከያ ሰራዊት የኢትዮጵያ ድንበር በመጣስ በጎንደር አብደራፊ አካባቢ በባለሃብቶች ይዞታ ላይ ጥቃት መፈጸሙን እማኞች ለኢሳት ገልጹ። ከቀናት በፊት ወታደሮች በባለሃብቶች የእርሻ ተቋማት ላይ በፈጸሙት ጥቃት ተሽከርካሪዎችና ግምቱ ከፍተኛ የሆነ ንብረት በእሳት ቃጠሎ ውድመት እንደደረሰበት ታውቋል።

ከ 20 እስከ 30 ኪሎሜትር የሚሆን የኢትዮጵያ ድንበር ጥሰው የገቡ የሱዳን ወታደሮች የፈጸሙት ድርጊት ምክንያት እንዳልታወቀና እርምጃው በአካባቢው ነዋሪ ዘንድ ስጋት ፈጥሮ መገኘቱን እማኞች ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ አስረድተዋል። ለጊዜው በሰዎች ላይ ስለደረስ ጉዳት የታወቀ ነገር አለመኖሩን የገለጹት ነዋሪዎች፥ ለወታደሮች ጥቃት ከኢትዮጵያ ወገን የተሰጠ ምላሽ አለመኖሩን አስታውቀዋል።

የሱዳን ወታደሮች እና ታጣቂዎች ተመሳሳይ ድርጊትን ከዚህ በፊት ሲፈጽሙ እንደቆዩ የገለጹት እማኞች፥ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በቅርብ ርቀት ቢገኝም ምንም አይነት አጸፋ አለመውሰዱ በነዋሪዎች ዘንድ ቅሬታ ማሳደሩም ታውቋል። በሁለቱ ሃገራት መካከል ተፈጽሟል የተባለውን ድንበር የማካለል ስምምነት ተከትሎ የሱዳን የጸጥታ ሀይሎች በአካባቢው ተመሳሳይ ጥቃት ሲፈጽሙ መቆየታቸው የሚታወስ ነው።

ከዚህ በፊት አብደራፊ በተፈጸመ ተመሳሳይ ድርጊት በአካባቢው ሰፍሮ የሚገኘው የመንግስት የፀጥታ ሃይል የአካባቢው ነዋሪ ምንም አይነት እርምጃ እንዳይወስድ ሲያሳስቡ መቆየታቸውን ከእማኞች ለመረዳት ተችሏል። በሰሞን (ቅዳሜ) ድንበር በመጣስ በሱዳን ወታደሮች ተወስዷል ስለተባለው ወታደራዊ እርምጃ ከኢትዮጵያ ወገን የተሰጠ ምላሽ የለም።

የኢትዮጵያ ባለስልጣናት በሁለቱ ሀገራት ተፈጽሟል የተባለውን የድንበር ስምምነት ተከትሎ ምንም አይነት መሬት ለሱዳን እንዳልተሰጠ ሲያስተባብሉ መቆየታቸው ይታወቃል። የተፈጸመውም ስምምነት ከዚህ በፊት የነበሩ መንግስታት የፈጸሙት ውል ነው ሲሉ ባለስልጣናት ገልጸዋል።

ሁለቱ ሃገሮች የፈጸሙት የድንበር ስምምነት በርካታ ለም መሬትን ለሱዳን የሚሰጥ ነው በማለት የኢትዮጵያ ድንበር ኮሚቴን ጨምሮ የተለያዩ ኢትዮጵያውያን ድርጊቱን ሲቃወሙ መቆየታቸውም የሚታወስ ነው።

በአብደራፊ ተፈጽሟል የተባለውን ጥቃት አስመልክቶም የሱዳን መንግስት የሰጠው ምላሽ የለም።

ምንጭ፤-ኢሳት
ኢሳት የኢትዮጵያውያን አይና ጆሮ ነው
ኢሳትን ይርዱ


No comments:

Post a Comment