Thursday, June 18, 2015

በባህር ዳር ከተማ ለመኖሪያ ቤት ባለ ይዞታዎች ተሰጥቶ የነበረው የባለቤትነት ማረጋገጫ ሰነድ ተመልሶ ተሰበሰበ

ሰኔ ፲ (አስር) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የምርጫ 2007 ቅስቀሳን ተንተርሶ በህዝቡ ዘንድ የሚቀርቡትን ጥያቄዎች ለመመለስ በሚል ሲንቀሳቀስ የነበረው ኢህአዴግ፤ በከተማዋ በልዩ ልዩ ክፍለ ከተሞች ለረዢም አመታት ለኖሩ የይዞታ ባለመብቶች ከምርጫው በፊት ሰጥቶት የነበረውን በባለ ቀለም የብአዴን አርማና የኢትዮጵያ ሰንደቃላማ ያሸበረቀ የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ መልሶ በመውሰድ ውሳኔውን ለመሻር እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡

ኢህአዴግ “በየክፍለ ከተማው ከ380 በላይ አባወራዎችን የይዞታ ማረጋገጫ በመስጠት የመኖሪያ ቤት ባለቤት አድርጌአለሁ፡፡” በማለት በመገናኛ ብዙሃን የምርጫ ቅስቀሳ ሲያካሂድ ቆይቷል። ይዞታችሁ ጸድቆላችኋል የተባሉ የህብረተሰቡ ክፍሎች ደስታቸውን ሲገልጹ ቢቆዩም፤ ምርጫው ካለቀ በኋላ ግን “የተሰጠው የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ ችግር ስላለበት እንደገና መመርመር አለበት” በሚል ሰነዱን ገቢ እንዲያደርጉ ታዘዋል።

በርካታ ነዋሪዎች ለክልል ሪፖርተራችን እንደገለጹላት ባሳለፍነው ሳምንት በግንቦት ሃያ ክፍለ ከተማ የይዞታ ቦታ ማረጋገጫ ሰነድ የተሰጣቸው ነዋሪዎች፣ ቤት ለቤት በመዘዋወር ሰነዱን ይዘው ወደ ክፍለ ከተማው ጽሕፈት ቤት በመሄድ እንዲያሰተካክሉ በገዢው መንግስት ካድሬዎች ሲዋከቡ ነበር።

በግንቦት ሃያ እና በሌሎች ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆኑ ባለ ይዞታዎች ከዓመታት በፊት በከተማዋ መሃል ነዋሪዎች የነበሩ ሲሆን፣ በቤት ክራይ በመማረር እና ተከራይተው ሲኖሩበት የነበረው የቀበሌ ቤት ለባለሃብቶች በመሸጡ ምክንያት ከከተማው ዳርቻ ወጣ በማለት መሬት ከገበሬዎች እየገዙ ከ1985 ዓ.ም ጀምሮ አዳዲስ ቤቶችን ገንብተው ይኖራሉ።

የገዢው መንግስት ካድሬዎች በየክፍለ ከተማው የሚያደርጉትን የምረጡኝ ቅስቀሳ ሙሉ በሙሉ ባሸናፊነት ለመወጣት በሚል ነዋሪውን ለማታለል የፈጠሩት ዘዴ መሆኑን የሚናገሩት አስተያየት ሰጪዎች፤ ካድሬዎች በግንቦት ሃያ ክፍለ ከተማ የጀመሩትን የይዞታ ቦታ ሰነድ ንጥቂያ በመቀጠል በበላይ ዘለቀ፣በህዳር 11 እና በሽምብጥ ክፍለ ከተማዎች በቀጣዩ ሳምንታት በማስፋፋት ለምርጫ መቀስቀሻ የሰጡትን የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ በተከታታይ እንደሚነጥቁ ምንጮች ገልጸዋል።

ከምርጫ በፊት ባደረጉት ቅስቀሳና በየመንደሩ በተደረጉ ልዩ ልዩ የማግባቢያ የቡና ጠጡ ዝግጅቶች የህብረተሰቡን ድምጽ ሙሉ በሙሉ እናገኛለን ብለው የገመቱት ካድሬዎች፣ ህብረተሰቡ ያልተጠበቀ ምላሽ ማሳየቱ ሳያበሳጫቸው አልቀረም ስትል አስተያየቱዋን አስፍራለች።


No comments:

Post a Comment