ክንፉ አሰፋ
አሁን የምጽፈውን በደንብ አንብቡ። መቶ በመቶ እውነተኛ ነው። እውነተኛ ኩሸት።
“ያልተገባ ነገር እየፃፍን ልጆችን አንጉዳ። ሕጻናት የምታስቡት ፕሮጀክት የተቀደሰ ነው። እንደሚሳካም እምነቴ የፀና ነው። አሁን ዋናው ጉዳይ ህጻናት ህልማቸውን እንድናሳካ የማበረታታትና የመደገፍ ነው። ሕጻናት ሆይ 20 ሚሊዮን ዶላር ባትይዙም ቢሮዬ ብቅ በሉ!”
አይቴ ቴድሮስ በፌስ ቡክ ገጻቸው የለቀቁት መልእክት ይህ አልነበረም። ይህ አሸባሪዎች በርዘው የለቀቁት እንጂ፣ የዶ/ር ቴድሮስ ትክክለኛው መልእክት እንዲህ ይነበባል።
“ያልተገባ ነገር እየፃፍን ልጅቷን ባንጐዳ፡፡ ያሰበችው ፕሮጀክት የተቀደሰ ነው እንደሚሳካም እምነቴ የፀና ነው፡፡ አሁን ዋናው ጉዳይ በሪቱ ጃለታ አሕመድ ህልሟን እንድታሳካ የማበረታታትና የመደገፍ ነው፡፡ Galatoomaa በሪቱ፡፡ አላህ ይባርክሽ፡፡ Rabbi si haaeebbisu በርቺ፡፡ Jabaadhuu”
በማህበራዊ ድር-ገጾች ብዙ ፉገራዎች ከተራው ሰው ሲሰራጩ ቢታዩም፤ ነጭ ፉገራን በሚንስትር ደረጃ ስናይ ግን የመጀመርያው መሆኑ ነው።
በፌስቡክ ላይ “የጀርመን ነዋሪ ነኝ” ያለችው ልጅ ፒያሳ ባር ስታስተናግድ ተገኘች። የፌስቡክ ጓደኞችዋ በድንገት ሲያገኟት ልጅት ምንም አልመሰላት። “ለምን ዋሸሽ?” ቢሉዋት። አይኗን በጨው አጥባ መልስ ሰጠች።
“መዋሸት ብርቅ ነው እንዴ?” አለች። የሷን ፉገራ በመቶ እጅ የሚበልጡ ፉገራዎች ስለሚያጽናኗት ቅንጣት ያህል አልደነገጠችም። ጣትዋን በቴድሮስ አድሃኖም ላይ እያነጣጠረች ጓደኞችዋን አረጋጋች።
የዚህችን ወጣት ውሸት ማካበድ እንደማያስፈልግ የተረዱት ጓደኞችዋ፣ ከውቅያኖስ የጠለቀውን፣ ከባህር የሰፋውን የቴድሮስ ውሸት ከሰሙ በኋላ ነበር።
“አበስኩ ገበርኩ… የባሰ አታምጣ።” ይላሉ እናቶች።
በአጼ ምኒሊክ ግዜ ለፍርድ ሙግት የቀረበ አንድ ሰው እጁን እያወራጨ ሲናገር ብብቱ ይታይ ነበር። እብብቱ ስር ያለ ጸጉሩም አጎፍሮ ነበር። የብብቱን ጸጉር ያስተዋሉ ዳኛ፣ ችሎት በመድፈር ወንጀል 50 ጅራፍ ቀጡት። ሰውየው ቅጣቱን ሳይግደረደር ተቀበለ። ይህንን 50 ጅራፍ ለምን ሳይከላከል እንደተቀበለ በጓደኛው ሲጠየቅ፣ ለብብቴ 50 የቀጡኝ የታችኛውን (የሃፍረተ ስጋዬን) ጎፈር ቢያዩ 100 ይሉኝ ነበር አለ።
“… የባሰ አታምጣ።” ነው ነገሩ።
ከዚህች ተራ ወጣት የባሰው ነጭ ውሸት በተጋለጠ ጊዜ፣
“የ14 አመትዋ ልጅ በአውስትራሊያ የ8ኛ ክፍል አስደናቂ ውጤት በማምስመዝገብ ያገኘችውን 20 ሚሊዮን ዶላር በኢትዮጵያ ለልማት ለማዋል ወሰናለች ያልኩት ፍጹም ስህተት ነው። ስለ ጥፋቴ የኢትዮጵያን ህዝብ ይቅርታ እጠይቃለሁ።” ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ተናገሩ።
የሚል ዜና ብንጠብቅ፣ ብንጠብቅ፣ ብንጠብቅ እስካሁን ልንሰማ አልቻልንም። አቤ ጎርጉሮ ያወጣውን ቅሌት በፌስቡክ ከተለቀቀው የልደት ውስኪያቸው ጋር አወራርደውታል። ውሸቱ አሸማቆ፣ አሸማቆ፣ ይገድላቸዋል… ድንጋጤው ይጥላቸዋል ብሎ የገመተ ጥቂት አይደለም። ግን እንዴት አይነት ፈጣጣ ናቸው። ያንን ጉድ ይዘው ቢሮ ሲገቡ ምንም እንዳልተፈጠረ መስለው ብቻ አይደለም። ውሸታቸውን ስልቅጥ፣ዋጥ አድርገዋት ሌላ ጥፋት ደረቡበት።
“ህጻናትን ወደኔ ይመጡ ዘንድ አትከልክሏቸው።” የሚለውን የክርስቶስ ጥቅስ ቀየር አድርገው የራሳቸውን ፈንጠዝያ ሊነግሩን ሞከሩ።
“…ህፃናትና ታደጊዎች የዋሆች እንደሆኑ ክፋት እንደሌላቸው ከኔ ጋር የምትስማሙ ይመስለኛል። በዚህ ምክንያትም ህፃናትና ታዳጊዎች የሚነግሩኝን ማመን እመርጣለሁ። ስህተትም ቢኖራቸው ከየዋህነት ካልሆነ ከክፋት አይመነጭም። ህፃናትን ማመን ስህተት ከሆነ መሳሳትን እመርጣለሁ።…”
አይቴ ቴድሮስ በዚያ በልካቸው ባልተሰራ ወንበር ላይ ተቀምጠው ከሰሞኑ በርካታ ህጻናትን እንደሚያስተናግዱ ይጠበቃል። ከውጭም ከሃገር ውስጥም ኢቨስተር ህጻናት ወደ ቴድሮስ ቢሮ ይጎርፋሉ። በሚሊዮን እና በቢሊዮን ዶላር ኢንቨስት እናደርጋለን ብለው ይዋሻሉ። ቴድሮስም በፌስ ቡክ ገጻቸው ታሪኩን ይለቀልቁልናል…ውሸቱንም ይለቁልናል። እነሆ ህጻናትን ማመን ስህተት አይደለምና እንዲዋሹ ተፈቅዶላቸዋል።
አፍ ሲከፈት ጭንቅላት ይታያል የሚባለው እውነት ነው። ጭንቅላት ሲገለጥ ደግሞ ገመና ይወጣል። በህወሃት መዋሸት አዲስ ነገር አይደለም። ሰዎቹ በቀን ከመቶ ግዜ በላይ ይዋሻሉ። በስነልቦና ተመራማሪዎች እነዚህን ሰዎች ፓቶሎጂካል ውሸታሞሽ ይላቸዋል። ይህ በሽታ ሰዎች ካሉበት ችግር ለማምለጥ ወይንም ከተቆራኛቸው የበታችነት ስሜት ይመጣል። ውሸት መናገር፥ አንዳች ጥቅም ለማግኘት ሲባል ሆን ተብሎ የሚፈፀም ድርጊት ነው። ለዚህ የስነ ልቦና ችግር ከጥቅሙ ይልቅ የረጅም ጊዜ ጉዳቱ ያመዝናል። የሚዋሸው ሰው በሰዎች ዘንድ የሚኖረውን ተቀባይነትን የሚያሳጣ ስብዕናም ያላብሳል። ችግሩ የስነልቦና ነውና መፍትሄውም የስነ-ልቦና ህክምና ነው።
አንድ አባት ልጁን ይጠራውና “ልጄ፣ ጥፋት ካጠፋህ የቤታችን ውሻ ስለሚነግረኝ ተጠንቀቅ።”ይለዋል። ልጁ ውሻ የሚሰማ እና የሚናገር ይመስለው ኖሮ ውሻውን እየቀረበ ያናግረው ነበር። ነብስ እስኪዘራ ድረስም ይህንን ውሽት አምኖ ተሸወደ።
የቴዎድሮስ አድሃኖም ግን ተገላቢጦሽ ሆነብን። ነብስ እስኪዘራ ድረስ… ህዝቡን መሸወድ ተያይዞታል። በዚህ የመረጃ ዘመን ነጭ ውሸት ዋሽቶ ሲያበቃ፣ ውሸቱ ሲነቃ ሌላ ታሪክ መፍጠር ህዝቡን ዝቅ አድርጎ መመልከት አይመስልም? 20 ሚሊየን ዶላር እኮ ከ20ሺ ዶላር ይበልጣል። 20 ሚሊዮን ዶላር ከ 200 ሺም ይበልጣል። 20 ሚሊዮን ከ 2 ሚሊዮንም በ10 እጥፍ ይበልጣል። 20 ሚሊዮን በጣም ተጋነነ። ከአንድ ጀምረው ቀስ በቀስ እያሳደጉ ወደዚያ ቢደርሱም አንድ ነገር ነው።
ጃፓኖች እንዲህ ይላሉ። “የሚታመን ውሸት ለመዋሸት ከፈለግህ የማይታመን እውነት አትናገር።”
አይቴ ቴድሮስ በቅድሚያ ውሸትን በማንኪያ… ውሸትን በትንሹ ያለማምዱን! … ታዲያ እንደጀመሩ ይጨርሱልን።
No comments:
Post a Comment