Monday, March 2, 2015

የግንቦቱን ምርጫ ለመታዘብ ከመንግስት ግብዣ እንዳልቀረበለት የአውሮፓ ህብረት ገለፀ

የግንቦቱን ምርጫ ለመታዘብ ከመንግስት ግብዣ እንዳልቀረበለት የገለፀው የአውሮፓ ህብረት፣ ባለፉት ሁለት ምርጫዎች በታዛቢዎቼ የቀረቡ ሪፖርቶች በኢትዮጵያ መንግስት ተቀባይነት ማጣታቸውም ከታዛቢነት እንድርቅ ገፋፍቶኛል አለ፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በ1997 እና 2002 ምርጫዎች የህብረቱን የትዝብት ሪፖርት ሙሉ ለሙሉ ሳይቀበለው መቅረቱ፤ ለዘንድሮ ምርጫ ሌላ የታዛቢ ቡድን የማሠማራትን ጥቅም አጣራጣሪ እንዲሆን አድርጓል ብሏል – የአውሮፓ ህብረት፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ፤ የአውሮፓ ህብረት በታዛቢነት አለመሳተፉ በምርጫው ተአማኒነት ላይ የሚያወጣው ለውጥ የለም ብሏል፡፡
ጠ/ሚ ኃይለማርያም ደሣለኝ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ የአውሮፓ ህብረት በራሱ ምክንያት ምርጫውን እንደማይታዘብ ማሣወቁን ጠቁመው፤ ምርጫውን የአፍሪካ ህብረት፣ የአገር ውስጥ ሲቪል ማህበራትና ተቋማት ይታዘቡታል ብለዋል፡፡
በአና ጐሜዝ የሚመራው የአውሮፓ ህብረት ታዛቢ ቡድን በ97 ዓ.ም የተካሄደውን ምርጫ ክፉኛ በመተቸቱ ከፍተኛ ውዝግብ ከመፈጠሩም በተጨማሪ፣ በ2002 ምርጫም ህብረቱ የምርጫው እለት ሂደቱ መልካም የነበረ መሆኑን ከገለፀ በኋላ፣ በጥቅሉ ምርጫው በአለማቀፍ መመዘኛዎች ሲፈተሽ ግን በርካታ ጉድለቶች አሉበት በማለት ሪፖርት ማቅረቡ ይታወሳል፡፡


No comments:

Post a Comment