Friday, March 6, 2015

በደልጊ ከተማ ከቤተክርስቲያን ማፍረስ ጋር በተያያዘ በተነሳ ተቃውሞ በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደረሰ

የካቲት ፳፯(ሃያ ሰባት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በሰሜን ጎንደር ጣቁሳ ወረዳ ደልጊ ከተማ ለቤተክርስቲያን ማሰሪያ የተከለለውን ቦታ 40 የሚሆኑ የምክር ቤት አባላትና ደጋፊዎቻቸው መከፋፈላቸው የፈጠረው ህዝባዊ ቁጣ፣ የካቲት 27 ጧት ላይ ወደ ተቃውሞ ተቀይሮ የከተማው ፖሊስ ጣቢያ ፣ መዘጋጃ ቤት፣ መስተዳድሩና የብአዴን ጽህፈት ቤት መስኮቶችና በሮች ከፍተኛ ጉዳት ሲደርስባቸው፣ ሁለት ፖሊሶችና አንድ የመዘጋጃ ቤት ዘበኛም ተደብድበዋል።
በብዙ ሺ የሚቆጠር ህዝብ የተሳተፈበትን ተቃውሞ ለማብረድ ፖሊሶች ጥይት ከመተኮሳቸውም በተጨማሪ ሰለፈኞችን በዱላ ደብድበዋል።
ለተቃውሞው መነሻ የሆነው፣ ህዝቡን ወክለው ሲከራከሩ የነበሩት አቶ ተችሎ ካሴና አቶ ፈንታ መኳንንት ተይዘው መታሰራቸው ሲሆን፣ ህዝቡ መሪዎቻችንን ፍቱልን በማለት ወደ ፖሊስ ጣቢያ አምርቷል። ፖሊስ ለህዝቡ ጥያቄ መልስ ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆኑ ህዝቡ
በጣቢያው ላይ ድንጋይ መወርወር መጀመሩን የአይን እማኞች ገልጸዋል
የህዝቡ ተቃውሞ እያየለ መምጣት ያሰጋው ፖሊስ፣ ሁለቱን የህዝብ ወኪሎች ከእስር ቤት በመልቀቅ፣ ችግሩን ለማብረድ ችሎአል። ህዝቡም ወኪሎቹን ተሸክሞ በከተማው በአሸናፊት ስሜት ሲጨፍር ማምሸቱን ነዋሪዎች ለኢሳት ገልጸዋል።
ከዚህ በሁዋላ የቤተ ክርስቲያኑዋ መሬት ይወሰዳል የሚል እምነት እንደሌላቸው የሚናገሩት ነዋሪዎች፣ የካቢኔ አባላቱ በዘረፋቸው የሚገፉበት ከሆነ ተመሳሳይ ተቃውሞ ይጠብቃቸዋል ብለዋል።


No comments:

Post a Comment