Friday, March 6, 2015

ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት አበል ካልተሰጠን ፍርድ ቤት አንቀርብም አሉ

የካቲት ፳፭(ሃያ አምስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በከሳሽ ኣቃቤ እና ህግ በተከሳሽ አቶ ኣስገደ ገ/ሥላሴ መካከል ሲደረግ በነበረው ክርክር ለምስክርነት የተጠሩት ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ሊቀርቡ ባለመቻካቸው በፖሊስ ተይዘው እንዲቀርቡ ቢታዘዝም፤ ባለስልጣናቱ ከለመዱት ምቹ ህይወት አኳያ ማቅረብ ሳይቻል ቀረ።
የህወሀት የደህንነት ሰራተኛው ብስራት አማረ የመሰረተባቸውን ክስ ተከትሎ ላለፉት ሶስት ዓመታት ሲከራከሩ የቆዩት የቀድሞው የህወሀት ታጋይና የአሁኑ የሰማያዊ ፓርቲ አባል አቶ አስገደ ገብረስላሴ ላይ ክሳቸውን እንዲከላከሉ በፍርድ ቤት ብይን መሰጠቱ ይታወቃል።

ይህን ተከትሎ አቶ ኣስገደ ከጠሩዋቸው የመከላከያ ምስክሮች ውስጥ አራት ከፍተኛ የህውሃት አመራሮችና ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ይገኙበታል። ለምስክርነት የተጠሩት እነኚህ ባለስልጣናት እነ አቶ ስብሃት ነጋ፣ አቶ ኣባይ ፀሃዬ፣ አቶ ስዩም መስፍን እና አቶ ኣርከበ ዕቁባይ ናቸው።
ባለስልጣናቱ ለመጁመሪያ ጊዜ ለ የካቲት 6 ቀን /2007 ዓመተ ምህረት የመከላከያ ምስክርነታቸውን ለመስጠት እንዲቀርቡ ትእዛዝ ቢደርሰዋቸውም ፤ እዚያው መቀሌ ከተማ ውስጥ እያሉ የዳኛውን ትእዛዝ በማጠፍ ሳይቀርቡ መቅረታቸውን አቶ አስገደ ገልጸዋል።
እንደገና ለሁለተኛ ጊዜ ለየካቲት 13 ቀን 2007 ዓመተ ምህረት በፖሊስ እንዲቀርቡ ዳኛዋ ቢያዙም፤ በድጋሚ እዚያው መቀሌ እያሉ የሉም ተብለው ሳይቀርቡ ይቀራሉ።
ለ3ኛ ጊዜ ለየካቲት 24 ቀን 2007 ዓ/ም በፖሊስ ተይዘው እንዲቀርቡ ሲታዘዝ ፖሊስ ቅድመ ሁኔታ ማቅረቡን ያመለከቱት አቶ አስገደ፤ ከቅድመ ሁኔታዎቹም አንዱ ተጠርተው ሲመጡ ከፍተኛ የሃገር ባለስልጣናት ከመሆናቸው አኳያ በሸራተን አዲሰ ደረጃ ባለ ሆቴል ማረፍ ስላለባቸውና በመቀሌ ያለው የዚያ ተመሳሳይ ሆቴል “ፕላኔት ሆቴል” በመሆኑ፤ ምስክር ጠሪው አቶ አስገደ በፕላኔት ሆቴል ለየአንዳንዳቸው ከነ ሁለት ኣጃቢዎቻቸው የአልጋ ዋጋ ሊከፍሉ ይገባል የሚል እንደሆነ ገልጸዋል።
ባለስልጣናቱ ከዚህም በተጨማሪ በከፍተኛ ፕሮቶኮል ማለትም በቪ አይ ፒ ደረጃ የኣየር ትኬት ከነ ኣጃቢዎቻችን ለመቁረጥ የሚያስችለን ገንዘብ፣ መቀሌ ለምንቆይበትም ቀናት የውሎ አበል ታስቦ ካልተሰጠን አንመጣም ብለውኛል ብሎ ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ በጽሁፍ ሪፖርት ማቅረቡን አቶ አስገደ ገልጸዋል። bአቶ አስገደ አስተያየታቸውን ሲያጠቃልሉ፦<<እዚህ ላይ የፖሊስ ሃላፊነት ምን መሆን ነበረበት? ተይዞ ይቅረብ የተባለው ድሃ ሰው ቢሆን ንሮ ምን ያጋጥመው ነበር?በኢትዮጰያ የህግ የበላይነት ተረጋግጧል ማለት ይህ ነውን?በማለት በ አጸንኦት ጠይቀዋል።


No comments:

Post a Comment