ሐምሌ ፩( አንድ ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ባህርዳር ሙሉዓለም አዳራሽ ሃምሌ 30/ 08 ዓ.ም በተደረገው የምስጉን መምህራን ሽልማትአሰጣጥ ላይ የተገኙ መምህራን፣ ሽልማቱ የተሰጠው በብአዴን ፓርቲ ውስጥ አባል በመሆን አስተዋጽዎ ላበረከቱት እንጅ በሙያቸው ላገለገሉት አይደለም በማለት ቅሬታቸውን ገልጸዋል።
መምህራኑ እንደተናገሩት ሽልማት የተሰጣቸው በስራቸው ታታሪ ለሆኑ መምህራን ሳይሆን በገዥው ፓርቲ ውስጥ አባል በመሆን ለተንቀሳቀሱ መምህራን ብቻ ነው። በተካሄደው የሽልማት አሰጣጥ ፕሮግራም ሁሉም የባህርዳር አስተዳደር መምህራን እንዲገኙ ጥሪ ቢተላለፍም፣ ከድርጅቱ አባላት ውጭ የተገኙ በጣት የሚቆጠሩ መሆናቸውን የተናገሩት ቅሬታ የተሰማቸው መምህራን፤ የክልሉ መንግስት የመምህራንን የሙያ ማህበር በራሱ አባላት በመሙላት የተለያዩ ጥቅማ ጥቅም በሚሰጥበት ጊዜ ለፓርቲው ታማኝ የሆኑትን ብቻ በመምረጥ የታታሪ መምህራንን ሞራል ሲነካ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
የክልሉ መንግስት በቅርቡ በአመራሩ ልቡ የሻከረውን መምህር ልብ ለማግኘት ‹‹ ለመምህራን ቤት እንሰራለን! ›› የሚል መግለጫ በመገናኛ ብዙሃን ቢሰጥም፣ አሁንም በቅድሚያ ሊስተናገዱ የሚችሉት የድርጅት አባላት ሊሆኑ እንደሚችሉና ከጊዜ በኋላም ምክንያት ፈልጎ ብዙሃኑን መምህር ሳያስተናግድ ይቀራል የሚል ስጋታቸውን አክለው ተናግረዋል፡፡
No comments:
Post a Comment