በወረዳ አንድ የሁለት ፖሊሶችንና የአንድ ወረዳ አስተዳዳሪን ህይወት ጨምሮ፣ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ዜጎች የተገደሉትን የቤት ማፍረስ ዘመቻ ለመደበቅ መንግስት ጥረት ቢያደርግም ቤታቸው የፈረሰባቸውን ዜጎች ህይወት የሚያሳዩ ፎቶዎች በማህበራዊ ሚዲያዎች እየተለቀቁ ነው።
የፌደራል ፖሊሶች አካባቢውን አጥረው ምንም ሰው ወደ ውስጥ እንዳይገባ ጥረት ሲያደርጉ ሰንብተዋል። ይህን ተከትሎም አሽከርካሪዎች በመንገድ መጨናነቅ ሲቸገሩ ሰንብቷል። ነዋሪዎች እንደሚሉት መስተዳድሩ ድርጊቱ እንዳይታወቅበት ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል። ሆኖም የመስተዳድሩ አስከፊ እርምጃ ከመጋለጥ አላመለጠም።
በሌላ በኩል ቤታቸውን የፈረሰባቸው ሰዎች በፖሊሶችና በመስተዳደሩ ሰራተኛ ላይ በወሰዱት እርምጃ እንዲወገዙ አንዳንድ የመንግስት ደጋፊ ጋዜጦች እየጻፉ ነው። ይሁን እንጅ ከነዋሪዎች ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው አስተዳዳሪው ህዝቡን ሰብስቦ ንግግር በሚያደርግበት ወቅት፣ ከህዝብ ጥያቄ ሲበዛበት “ ከሃና ማርያም በታች ያለውን ቆሻሻ ማጽዳት ግዴታዬ ነው” ብሎ ህዝብን በቆሻሻ መስሎ በመናገሩ የህዝቡን ቁጣ እንደጨመረውና ለእርምጃው ምክንያት ሆኗል።
ሟቹ አስተዳዳሪ ከቤታቸው ከፈረሰባቸው ግለሰቦች በጉቦ መልክ እስከ 6 ሺ ብር ይቀበል እንደነበርና ሁኔታው ያስገረማቸው ነዋሪዎች “ የዚህ ሁሉ ህዝብ ገንዘብ አንተ ባንክ አካውንት ውስጥ የለም?” ሲሉ ጠይቀውት እንደነበርና በዚህ ተበሳጭቶ “ ቆሻሻ” ብሎ እንደሰደባቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል።
ሟቹ አስተዳዳሪ በአዲስ አበባ ውስጥ አንድ ቪላ ቤት እና ሌላ አንድ ሁለት ደረጃ ያለው ቤት እንደነበረው ታውቋል።
No comments:
Post a Comment