ሐምሌ ፰ ( ስምንት ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በደቡብ ሱዳን ያገረሸውን ግጭት ተከትሎ የውጭ አገር ዜጎች በየአገሮቻቸው ኢምባሲ አማካኝነት አገሪቱን ለቀው በመውጣት ላይ ቢሆንም ኢትዮጵያውያን ግን ተመሳሳይ እርዳታ ባለማግኘታቸው ደህንነታቸው አደጋ ውስጥ ወድቋል። የአውሮፓ ሕብረት አገራት ዜጎችን ጨምሮ የአፍሪካ አገራት በተለይም ጎረቤት ኡጋንዳና ኬንያ ወታደሮቻቸውን ወደ ደቡብ ሱዳን በመላክ ዜጎቻቸውን ከጥቃት በመከላከል ወደ አገራቸው እየመለሱ ነው።
ድጋሜ ባገረሸውን የአገሪቱን የእርስ በርስ ግጭት ተከትሎ ዋና ከተማዋ ጁባን ጨምሮ በመላው ደቡብ ሱዳን ውስጥ በንግድና አገልግሎት ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ኢትዮጵያዊያን ዜጎች ላይ ጥቃት እየደረሰ ነው። እስካሁን በኢትዮጵያዊያኑ ላይ የንብረት ዝርፊያን ጨምሮ ግድያና አካላዊ ጥቃቶች ቢፈጸሙም ፣ ከገዢው ፓርቲ በኩል ለዜጎች ከለላ ለመስጠት ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ እየተደረገ አይደለም።
ቤት ንብረታቸው ሱቆቻቸው እየተዘረፉ ያሉት ዜጎችን ከጥቃት ለማዳን በደቡብ ሱዳን የተሰማራው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትና ኤንባሲው የኢትዮጵያዊያንን ሕይወት ለመታደግ ምንም ዓይነት እርምጃ አለመውሰዱ እንዳሳዘናቸው በምሬት ተናግረዋል። ኢትዮጵያዊያኑ አሁን ያሉበትን አስከፊ ሰቆቃ ተረድቶ ገዥው መንግስት ከለላ እንዲሰጣቸው ተማጽኖዋቸውን አሰምተዋል።
No comments:
Post a Comment