Monday, May 11, 2015

በጋምቤላ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት ሰዎች ተገደሉ

ሚያዝያ ፫ (ሦስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በጋምቤላ እና በደቡብ ክልል አዋሳኝ ከተሞች የሚታየው የጸጥታ ሁኔታ እየተበላሸ መሄዱን ተከትሎ ዜጎች እየተፈናቀሉና እየተገደሉ መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ።
ከሁለት ቀን በፊት ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች በጎደሬ ወረዳ በየሪ ቀበሌ በፈጸሙት ጥቃት 6 ሰዎች ሲገደሉ አንድ ሰው ደግሞ በጽኑ ቆስሎ ሆስፒታል ገብቷል። ሌሎች ወገኖች ደግሞ የማቾች ቁጥር 7 ነው ይላሉ። ይህንን ተከትሎ ዛሬ በሚጤ ከተማ የተቃውሞ
ሰልፍ የተካሄደ ሲሆን፣ የአካባቢው ነዋሪዎች ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ካልመጡ በስተቀር የቀብር ስነስርአት አንፈጽምም ብለዋል።
የተቃውሞ ሰልፉ ነገም እንደሚቀጥል የሚናገሩት ነዋሪዎች፣ ግጭቱ እየተባባሰ ሲሄድ መንግስት ከዳር ቆሞ እያየ ነው በማለት ይወቅሳሉ። ግችቱን ተከትሎ በርካታ ዜጎች እየተፈናቀሉ ወደ ከተሞች በመፍለስ ላይ መሆናቸውንም ነዋሪዎች ይናገራሉ።
ካለፈው መስከረም ወር ጀምሮ በቴፒና አካባቢዋ ያለው ግጭት ተባብሶ በመቀጠሉ ነዋሪዎች ከፍተኛ ስጋት ላይ መውደቃቸውንም ተናግረዋል። ዛሬ በከተማዋ ውስጥ የጥይት ድምጽ ይሰማ ነበር የሚሉት ነዋሪዎች፣ በርካታ ቁጥር ያላቸው የሸኮ መዠንገር ነዋሪዎች እየፈለሱ
ወደ ቴፒ ከተማ በመግባት ላይ መሆናቸውን ይገልጻሉ።
በአካባቢው የሚታየውን የእርሻ ቦታ ለመቆጣጠር ሲባል ግጭቶች ሆን ተብሎ እንደሚቀሰቀሱን የሚገልጹት ነዋሪዎች፣ በተለይም ጡረታ ወጡ ከፍተኛ የህወሃት የጦር መኮንኖች ሰፋፊ የእርሻ ቦታዎችን እየወሰዱ የአካባቢው ተወላጆች ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ ማድረጋቸው
ግጭቱን አባብሶታል።
ባለፈው አመት በዚሁ አካባቢ በተፈጠረ ግጭት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሲገደሉ፣ የመንግስት አቃቢ ህግ ለግችቱ መንስኤ ናቸው ባላቸው የአካባቢው ተወላጆች ላይ በከፈተው ክስ 75 ሰዎች መገደላቸውን ገልጿል።
ግጭቱን አስነስተዋል በሚል ከ30 በላይ የአካባቢው ባለስልጣናት ቢታሰሩም፣ ግጭቱ ግን ሊቆም አልቻለም።


No comments:

Post a Comment