በስልጣን ላይ ያለውን አገዛዝ በማንኛውም አማራጭ ለማስወገድ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኙ የተቃዋሚ ሃይሎች በጋራ ለመታገል የሚያስችላቸውን ውይይት መጀመራቸውን ለኢሳት በላኩት መግለጫ አስታውቀዋል። ውይይቱን የጀመሩት የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ( ትህዴን)፣ የጋምቤላ ህዝብ ነጻነት ንቅናቄ፣ የቤንሻንጉል ህዝብ ነጻነት ንቅናቄ፣ የአማራ ዲሞክራሲያዊ ሃይል ንቅናቄና አርበኞች ግንቦት7 ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ንቅናቄ ናቸው። ድርጅቶቹ ” በሂደት ወደ አንድ የምንመጣበትን ሁኔታ እያመቻቸን፣ አሁን ግን አገርና ህዝብን የማዳኑን ስራ እንጀምር በሚል ውይይት እያደረግን መሆናችንን ለኢትዮጵያ ህዝብ መግለጽ እንወዳለን” ብለዋል። የኢህአዴግን አገዛዝ በሃይል እናስወግዳለን በማለት የትጥቅ ትግል የሚያካሂዱ ድርጅቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ በሰው ሃይልና በሎጂስቲክ እየተጠናከሩ መምጣታቸውን የሚደርሱን መረጃዎች ያመለክታሉ። ስርዓቱ በአገር ውስጥ በሚገኙ ዜጎች ላይ እያደረሰ ያለው አፈና ከጊዜ ወደ ጊዜ መጨመር፣ ወጣቶች የትጥቅ ትግል አማራጭን የሚደግፉ ሃይሎችን እንዲቀላቀሉ እያደረጋቸው ነው።
No comments:
Post a Comment