ሚያዝያ ፳ (ሃያ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ሰሞኑን በመላው አገሪቱ በሚታየው የሕዝብ ቁጣ ስጋት ላይ የወደቀው ኢህአዴግ መራሹ መንግስት፣ በምርጫ ቦርድ አማካይነት ግንቦት 16 ቀን ሚካሄደው ሀገር አቀፍ ምርጫ በሠላም ስለሚጠናቀቅበት ለመምከር የአንድ
ቀን ስብሰባ ጠርቷል፡፡ በሒልተን ሆቴል በሚካሄደው ስብሰባ ላይ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እና የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች እንዲገኙ ተጋብዘዋል፡፡
በተቃዋሚዎች ሁልጊዜም ቅሬታ የሚቀርብበት ምርጫ ቦርድ በተለይ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የምርጫውን ውጤት ያለማንገራገር እንዲቀበሉ ለማግባባት ሙከራ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።
ኢትዮጵያዊያን በሊቢያ በረሃ በአይኤስ አሸባሪ ቡድን በግፍ መገደላቸውን ለመቃወም ባለፈው ሳምንት በመንግስት በተጠራው ሰልፍ ላይ ሕዝቡ በግልጽ ለኢህአዴግ መራሹ መንግስት ያለውን ጥላቻ ካንጸባረቀ ወዲህ በኢህአዴግ ካድሬዎችና አባላት ዘንድ ከፍተኛ
ድንጋጤ መፈጠሩ የታወቀ ሲሆን፣ ከምርጫው ውጤት ጋር ተያይዞ ሁከት ሊነሳ ይችላል የሚል ስጋት የኢህአዴግ አባላትን አስጨንቆአል፡፡ ነባር የኢህአዴግ አመራሮች ወደ ክልሎች በመሄድ ፣ ህዝቡን ለማረጋጋት ሙከራ በማድረግ ላይ መሆናቸውን የደረሰን መረጃ
ያመለክታል። ህዝቡ ግን አሁንም ምሬቱን እየገለጸ ነው
ኢህአዴግ በአገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶች ተቃውሞውን አስነስተውታል በማለት ውንጀላ ቢያሰማም ህዝቡ ግን የሚቀበለው አልሆነም። ለኢሳት የሚደርሱ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የፌደራል ፖሊሶች ተቃውሞውን ለመግለጽ በወጣው ህዝብ ላይ
የወሰዱት እርምጃ ፣ ህዝቡን ይበልጥ አስቆጥቷል፡፡ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማእከል ምርጫውን ተከትሎ ህዝባዊ አመጽ ይነሳል አይነሳም የሚል የህዝብ መጠየቂ ፎርም አሰራጭቶ በትኗል።
የፌደራል ፖሊስ ከ1 ሺ በላይ ወጣቶችን ይዞ ማሰሩን አምኖ፣ ይሁን እንጅ 150 ዎችን ብቻ አስቀርቶ ሌሎችን መፍፋቱን ገልጿል። ከተለያዩ የአዲስ አበባ አካባቢዎች የሚደርሱን መረጃዎች እንደሚያመለክቱት አሁንም ድረስ ወጣቶች እየታደኑ በመታሰር ላይ ናቸው።
ኢህአዴግ ያቋቋማቸው የወጣትና የሴት ሊግ አደረጃጀቶች ሰዎችን እየጠቆሙ በማሳሰር ላይ መሆናቸውን መረጃዎች አመልክተዋል።
በአገር ቤት የሚታየው ቁጣ በውጭ በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ላይም በተመሳሳይ ሁኔታ እየተንጸባረቀ ነው። በስዊድን በተደረገ የሻማ ማብራት ስነስርአት ላኢ እጅግ በርካታ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ተገኝተዋል። የተለያዩ የሃይማኖት አባቶችና የድርጅት መሪዎች
በሊቢያና በደቡብ አፍሪካ በሚገኙ ወገኖች ላይ የተፈጸመውን አሰቃቂ ግፍ አውግዘዋል። ለኢትዮጵያውያን ስደትና መከራ በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ተጠያቂ መሆኑንም ኢትዮጵያውያን ገልጸዋል።
በዴንቨር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም በአይ ሲሲ በግፍ የተገደሉትን ኢትዮጵያውያንን አስበዋል።
No comments:
Post a Comment