ሚያዝያ ፳፪ (ሃያ ሁለት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የኢሳት ምንጮች እንደገለጹት ፣ የማረሚያ ቤቱ ሹሞች ፖሊሶችን ለአስቸኳይ ስብሰባ እንደሚፈልጓቸው ከገለጹላቸው በሁዋላ፣ በስብሰባው ላይ የተገኙትን ፖሊሶች የሞባይል ስልኮች ተቀብለው ፍተሻ አድርገዋል።
በፍተሻው ወቅት 18 ፖሊሶች ከኢንተርኔት የተለያዩ ፎቶዎች፣ ጽሁፎችንና ቀስቃሽ ዘፈኖችን በማውረድ በስልኮቻቸው ላይ አስቀምጠው የተገኘ ሲሆን፣ ፖሊሶቹም ወዲያዉኑ እንዲባረሩ ተደርጓል። በተለይ የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ፎቶ ግራፍ በተገኘባቸው ፖሊሶች ላይ
ክስ ለመመስረት እንደታሰበ ለማወቅ ተችሎአል። ከዚህ ቀደም በተለያዩ አካባቢዎች በተደረጉ ፍተሻዎች ከ30 በላይ ፖሊሶች መንግስትን የሚያወግዙና የተቃዋሚ መሪዎችን ፎቶዎች ስልኮቻቸው ላይ አስቀምጠዋል በሚል ማእከላዊ እስር ቤት ውስጥ እንዲገቡ ሲደረግ፣ ሌሎች
ደግሞ ጃንሜዳ አካባቢ በሚገኝ እስር ቤት ውስጥ ታስረው ጉዳያቸው እየተጣራ ነው።
በስርአቱ የተማረሩ የፌደራል ፖሊሶች በብዛት በመጥፋት ላይ መሆናቸውንም የደረሰን መረጃ ያሳያል። ሰሞኑን በአዲስ አበባ ተካሂዶ በነበረው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ በርካታ የፌደራል ፖሊሶች ስራቸውን በአግባቡ አልተወጡም ተብለው እየተገመገሙ ነው። አብዛኞቹ ፖሊሶች
በህዝቡ ላይ እርምጃ ለመውሰድ ፍላጎት አለማሳየታቸው የመንግስት ባለስልጣናቱን አሳስቧል።
በሌላ ዜና ደግሞ መንግስት በአዲስ አበባ በ10ሩም ክ/ከተሞች በሚገኙ ወጣት መዝናኛ ማዕከላት መሰብሰቢያ አዳራሽ ነዋሪዎችን ሰብስቦ ባለፈው ሳምንት ራሱ በጠራው ሰልፍ ላይ የተሳተፉ ንጹሃን ዜጎችን ለማፈንና ለማሰር እንዲመቸው በወቅቱ የተቀረፀውን ቪዲዮ
በዲቪዲ በመክፈት በቴለቪዥን በማሳየት ከዚህ ቴሌቪዥን የምታዩዋቸውን ወጣቶች ጠቁሙ፣የማን ልጅ ነው፣ይህንን ወጣት የሚያውቅ ካለ መረጃ ለመሰብሰብ እየጣረ ነው።
ድርጊቱ በህብረተሰቡ መካከል መከፋፈልና ጠላትነትን ለመፍጠር ተብሎ እርስ በርስ በመጠቋቀም አንድነትን ለማፍረስ ያሰበው ሴራ ነው ሲሉ አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል።
የመንግስት ካድሬዎች ” በሰፈራችሁ ስራ የሌለው ልጅ ማንነው?” በማለት እየጠየቁ ሲሆን፣ አላማውም ምርጫው እስኪያልፍ ድረስ ከአዲስ አበባ ውጪ በማረሚያ ቤት አቆይቶ ለመልቀቅ ነው ሲሉ አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል።
እስካሁን በተጠየቁት ጥቆማዎች ህብረተሰቡ ልጆችን አሳልፎ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነም።
No comments:
Post a Comment