እነዚህ ወገኖቻችን ሰማዕታት ናቸው፡፡ ሃይማኖታቸውን አንለውጥም ብለው የተሠዉ፡፡ ‹ስደተኛ ኢትዮጵያውያን› የሚለውን አገላለጽ ነፍሴ ትጸየፈዋለች፡፡ ከአኩሪው የሰማዕትነት ተግባራቸው በላይ ስደተኛነታቸው ለማጉላት ስለሚያኮበኩብ፡፡ ሰው በሀገሩ ቢኖር፣ ቢሠራና ቢከብር የመጀመሪያ ምርጫው ነው፡፡ በተለይ ኢትዮጵያውያን፡፡ ነገር ግን ‹እልፍ ሲሉ እልፍ ይገኛል› ይባላልና የቸገረው ቢሰደድ ምን ይፈረድበታል? በርግጥ ስደቱ በሰላም፣ በሕግና በጤና ቢሆን የማይወድ የለም፡፡ ግን ሁል ጊዜ ይቻላል ወይ? ምቹ ሁኔታስ አለ ወይ? ዛሬ ከአውሮፓ፣ አሜሪካና አውስትራልያ፣ ከአፍሪካና እስያ ገንዘባቸውን እየላኩ አንዳንዴ ከቡና በላይ አንዳንዴም ከቡና ቀጥሎ የውጭ ምንዛሬውን የሚያስገኙልን ወገኖች አብዛኞቹ ዛሬ ‹ሕገ ወጥ› በምንለው መልኩ የሄዱ አይደለም ወይ? እንዲያ እንዲሆኑ ያደረጋቸውን መሠረታዊ ምክንያት መፍታት እንጂ የሆኑበትን መንገድ ማውገዝ ምን ይጠቅማል?
በሀገራችን ኢትዮጵያ እየኖሩ በአክራሪዎችና አሸባሪዎች ሕይወታቸው የተሠዉ ክርስቲያኖች አልነበሩም ወይ? በ1980ዎቹ መግቢያ በአሰቦት ገዳም የታረዱት መነኮሳት፣ በአርሲ ኮፈሌ የተገደሉትን ምእመናንና በ1998 ዓ.ም. በጅማ በሻሻ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ የተሠዉት ምእመናንና ካህናት ስደተኞች ሆነው አልነበረምኮ? ክርስቲያን ስለሆኑ እንጂ፡፡ በአይሲስ እጅ ወደቀው ከነበሩት መካከልኮ እነርሱ የእስልምና እምነት ይከተላሉ ብለው ያሰቧቸውን ሱዳናውያንና ሶማልያውያንን ያለ ምንም እንግልት ይለቋቸዋል፡፡ የቁርዐን ጥያቄ የሚጠየቁት ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ናቸው፡፡ ከእነርሱም መካከል ሙስሊም አይደለም ብለው ያሰቡትን ነው በኮንቴይነር አስገብተው ወደ አልታወቀ ሥፍራ የሚወስዱት፡፡ እነዚህም ቢሆኑ ምርጫ ይቀርብላቸዋል፡፡ ‹እስልምናን ወይንም ሞትን መቀበል› እምነታችንን አንለውጥም ሲሉ ይገደላሉ፡፡ አይሲስ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ክርስቲያኖችን ሲያርድ በግድ እንዲመለከት የተደረገው ኤርትራዊው የ16 ዓመት አዳጊ ወጣት ናኤል ጎይቶም ከእጃቸው አምልጦ ከወጣ በኋላ ለኢንተርናሽል ቢዝነስ ታይምስ የነገረውም ይሄንኑ ነው፡፡ ለቪኦኤ ቃሉን የሰጠው ከሞት ያመለጠ ወጣት ይህንኑ ያረጋገጠ ነበር፡፡ አይሲስም በአድራሻ ‹ጠላታችን ለሆነቺው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን› ብሎ ተናግሯል፡፡ አይሲስ ራሱ ሀገራዊ ብሔርተኝነትን ሳይሆን ሃይማኖታዊ ብሔርተኝነትን ማስፈን ነው ዓላማው፡፡ ሊመሠርትም የተነሣው ‹የእስልምናን መንግሥት› ነው፡፡
ይኼ ሁሉ የሚያሳየው እነዚህ ወንድሞቻችን የተሠዉት ክርስቲያን በመሆናቸው እንደሆነ ነው፡፡ በንግግራችንም ሆነ በመግለጫችን ልንናገረው የሚገባን እውነትም ይኼው ነው፡፡ ሕገ ወጥ ስደትን እንኳን እኛ ስደተኛው ራሱም አይፈልገውም፡፡ የሞታቸው ዋና ምክንያት ግን ስደት አይደለም፡፡ ያ ቢሆን አብረዋቸው የተሰደዱት ሶማልያውያንና ሱዳናውያንም ይገደሉ ነበር፡፡ ምክንያቱ ክርስትናቸው ነው፡፡ እነርሱን ‹ባይሄዱ ኖሮ አይገደሉም ነበር› በሚል ዓይነት ጥፋተኞች ለማድረግ ለምን እንደክማለን፡፡ እነርሱ የአቋም ሰዎች ናቸው፡፡ ዘላቂውን አቋም ለጊዜያዊ ጥቅም መቀየር ያልፈቀዱ፡፡
ስለ እነዚህ ወንድሞች ክርስትና መናገር ሌሎች አማኞችን ያስቀይማል ወይም ያገላል ብለን ከሆነ ስሕተት ነው፡፡ ሙስሊሞችና ሌሎችም ወገኖቻችን ‹ማንም በእምነቱ ምክንያት መገደሉን እናወግዛለን› እያሉኮ ነው፡፡ የትግራይ ክልል እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ርእሰ መንበር ‹በዲናችን አስተምሮና አሳምኖ እንጂ አስገድዶና ገድሎ እምነት ማስቀየርን አንቀበልም› ነው ያሉት፡፡ ይኼ ነገር እነዚህ ወገኖቻችን በግድ እምነታችሁን ቀይሩ ተብለው በአረመኔዎች መገደላቸውን እየነገሩን ነው፡፡
ከአይሲስ እጅ በእግዚአብሔር ቸርነት ለወሬ ነጋሪነት ያመለጡ ወገኖች እንደሚናገሩት አይሲስ ትልቁ ትኩረቱ በኢትዮጵያና ኤርትራ ስደተኞች ላይ ነው፡፡ ሱዳናውያንንና ሶማልያውያን ወዲያው ነው የሚለቀው፡፡ በተለይ ደግሞ የመስቀል ምልክት በሰውነታቸው ላይ የተነቀሱና ሌሎች ሃይማኖታዊ ምልክቶችን ያደረጉትን ወዲያው ያለምንም ጥያቄ ክርስቲያን መሆናቸው አረጋግጦ ለብቻ በኮንቴይነር ያስቀምጣቸዋል፡፡ ከአይሲስ ጋር የሚደረግ ውይይት፣ ድርድር፣ ክርክር የለም፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ የለበሱት የሊቢያ ወታደሮችን ልብስ ስለሆነ እነማን እንደሆኑ የሚታወቀው በኋላ ነው፡፡ የሰዎችን ጥያቄና ልመና ለማስተናገድ ዕድል የሚሰጡ አይደሉም፡፡
ከዚህ አንጻር ከኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ጋር ጀማል የተባለ ሶማልያዊ ሙስሊም ‹ክርስቲያኖችን እረዳለሁ ብሎ› አብሮ ተሠውቷል የሚለውን መረጃ ለመቀበል ይቸግራል፡፡ በመጀመሪያ ሶማልያውያንን ለጥያቄ አያቀርቧቸውም፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ጓደኞቼን ትቼ አልሄድም ስላለ አይሲስ ‹ና አብረሃቸው ሂድ› ብሎ አስተያየት የሚያደርግ ቡድን አይደለም፡፡ በሌላ በኩል ተጓዦቹ ሲያዙ የሊቢያ ወታደሮች እንደያዟቸው እንጂ አይሲስ መሆናቸውን የሚያውቁበት ዕድል የለም፡፡ የለበሱት የወታደር ልብስ ነው፡፡ የመጀመሪያው መለያየት የሚፈጠረው ደግሞ እምነትን ሳይሆን ዜግነትን መሠረት አድርጎ ነው፡፡ ሶማልያውያንና ሱዳናውያን ወዲያው ያስኬዳሉ ኤርትራውያንና ኢትዮጵያውያን ይይዛሉ፡፡ ሶማልያውያንና ሱዳናውያን የሚይዙት የተለየ እምነታቸውን የሚጠራጥር ነገር ካገኙባቸው ብቻ ነው፡፡ እንደ ማተብ፣ የመስቀል ንቅሳት፣ የአለባበስ ለውጥ ወዘተ፡፡ ክርስትና ጥያቄ ሆኖ የሚመጣው ከዚያ በኋላ ነው፡፡ በኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ዘንድ፡፡
በዚህ ሁሉ ነገር ጀማል ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖችን ለመርዳት ዕድል የሚያገኝበት መንገድ የለም፡፡ ቢፈልግ እንኳን፡፡ እርሱ ከሶማልያውያን ጋር መጀመሪያ ተለይቶ ወይ ሄዷል፤ ወይ ሌላ ቦታ ተቀምጧል፡፡ እስካሁን ለማምለጥ ዕድል ያገኙ ወገኖችም ይህንን ታሪክ አያውቁትም፡፡ መረጃውን ሰጡ የተባሉት የሶማልያ ምንጮች ናቸው፡፡ ተርፈው የወጡ ወገኖች የሚጠራጠሩት ሁለት ነገር ነው፡፡ አንድ ጀማል እምነቱን ቀይሮ ክርስቲያን ከሆነና ይህንንም ከመሰከረ፤ ሁለት በሰውነቱ ላይ የመስቀል ንቅሳት አሠርቶ ከሆነ፡፡ ከዚያ ውጭ ግን ሶማልያዊ ሙስሊም ሆኖ ከኢትዮጵያውያን ጋር የሚታረድበት በቂ ምክንያት ሊኖር አይችልም፡፡ እንኳን ለመታረድ አብሮ ለመቆየት ዕድል የለውም፡፡
ይኼ ማለት ሙስሊሞች ክርስቲያኖችን አይወዱም ወይም አይረዱም ማለት አይደለም፡፡ በሊቢያ ተደብቀው የሚገኙ ኢትዮጵያውያን መረዳዳቱን በሚገባ መስክረዋል፡፡ ይኼ የማይታበል ሐቅ ነው፡፡ ይኼ ነገር በራሱ ቆሞ ሊናገር የሚችል ስለሆነ ሌላ ነገር መፍጠር የሚያስፈልገው አይመስለኝም፡፡
ጀማልን በተመለከተ የተሠራጨውን ዜና መቶ በመቶ አይሆንም ማለት አይቻልም፡፡ በቦታው የለንምና፡፡ ከዓይን ምስክሮችና በሊቢያ ምድር ከሚገኙ ምንጮች፣ ተርፈውም ለመገናኛ ብዙኃን ምስክርነት ከሰጡ ሰዎች ተነሥተን ስናየው ግን ‹ተረጋግጦ ያለቀ እውነት ነው› ብሎ ለመቀበል የበለጠ መረጃ የሚያስፈልግ ይመስለኛል፡፡
እነዚህን ወገኖች ለማሰብ፣ ቤተሰቡን ለማጽናናት በቀጣይም ተመሳሳይ ነገር እንዳይከሰት ለመሥራት ቤተ መንግሥት፣ ቤተ ክህነት፣ ሚዲያዎች፣ ታዋቂ ሰዎች፣ የንግድ ተቋማትና ሌሎችም እያደረጉ ያለው ነገር ነገሩን በኢትዮጵያዊ ባሕልና ወግ መሠረት ለማከናወን የሚደረገውን ጥረት ያሳያል፡፡ በየእምነት ተቋማቱ ጸሎት እየተደረገ ነው፡፡ በየ አጥቢያው ምሕላ እየተከናወነ ነው፡፡ በኀዘንተኞቹ ቤት ሕዝቡ በነቂስ እየተገኘ ኀዘኑን እየተካፈለ ነው፡፡ ኀዘንተኞቹም በሕዝቡ አጋርነት እየተጽናኑ ነው፡፡ ፓርላማው ያወጀው የሦስት ቀን ብሔራዊ ኀዘን እየተተገበረ ነው፡፡ የሚስመሰግን ነው፡፡
የምናደርጋቸው ነገሮች ግን እምነቱንና ትውፊቱን፣ ወጉንና ባሕሉን፣ ኅሊናንና ሰብእናን የጠበቁ ቢሆኑ መልካም ይሆናሉ፡፡ ርዳታችን፣ ኀዘናችን፣ ማጽናናታችን፣ ችግሩን ለመፍታት መሯሯጣችን እምነት፣ ኅሊና፣ ባሕልና ወግ አስገድዶን እንጂ ለተወዳጅነትና ለገጽታ ግንባታ ባይሆን ይመረጣል፡፡ የወገኖቻችንን መሥዋዕትነት ለፖለቲካ ጥቅም፣ ለሚዲያ ፍጆታ፣ ሩኅሩኅነታችንን ለማሳያ፣ ለጋስነታችንን ለማስመስከሪያ እንድንጠቀምበት ኢትዮጵያዊ ባሕልና ወግ አይፈቅድልንም፡፡ የምንሰጠው ገንዘብ፣ የምንወስደው የእዝን እንጀራ፣ የምንደርሰው ልቅሶ ሁሉ እየተቀረጸ፣ በፎቶ እየተነሣ፣ በሬዲዮ እየተላለፈ የሚደረግ ከሆነ ለራሳችን ገጽታ ስንል እንጂ አዝነን ያደረግነው መሆኑን ያጠራጥራል፡፡ ሌሎች ስለ እኛ ይናገሩ እንጂ እንዴት ‹ይህን አድርገናል፣ ይህን ሰጥተናል› እያልን ራሳችንን ራሳችን እንቀርጻለን፣ ራሳችንንስ እንዴት ራሳችን እናስተዋውቃለን? ነውር ቀረ ማለት ነው? የንግድ ድርጅቶችና ‹ታላላቅ ሰዎች› ይህንን ለራስ መክበሪያነት ሲያውሉት ማየት ግን ያማል፡፡
አንዳንድ ሰዎችን አይተናል ረድተዋል፣ ልቅሶ ደርሰዋል፣ አጽናንተዋል፣ የሚችሉትን ሁሉ አድርገዋል፡፡ ነገር ግን ነጋሪት እየጎሰሙ አይደለም፡፡ በርግጥ በተራራ ላይ ያለች መብራት ልትሠወር ስለማይቻላት ሌሎች አይተዋቸው ስለ እነርሱ ዘግበዋል፡፡ እነርሱ ግን ‹እዩልን ስሙልን› አላሉም፡፡ ‹አምስት ሺ ብር ሰጠሁ፣ ዐሥር ሺ ብር ሰጠሁ› ሲሉ አልተሰሙም፡፡ ድርጊቱን የተደረገለትና ዋጋ ቆጣሪው አምላክ ያውቀዋል፡፡ በሚዲያ ገብተውም ‹እገሌ ይህንን ያህል ሺ ብር ስለሰጠዎት አመስግኑት› ብለው የኀዘንተኛ ምስጋና አልሰበሰቡም፡፡
ጎበዝ እየተስተዋለ እንጂ፤ አንገቱን ለሰጠ ገንዘብ ሰጥን ብለን ይሄ ሁሉ ነጋሪት?
No comments:
Post a Comment