Wednesday, April 1, 2015

የኮንዶሚኒየም ቤቶች ዋጋ ቤትፈላጊዎችን አስመርሯል


መጋቢት ፳፪(ሃያ ሁለት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የመጪውን ምርጫ መቃረብ ተከትሎ በአዲስአበባ ከተማ ለመጀመሪያ ጊዜ 32ሺ ያህል ብዛት ያለው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ ከሳምንት በፊት ቢወጣም

ቅድሚያ ክፍያው የዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች አቅም በላይ ሆኗል።

የኮንዶሚኒየም ቤቶች ዋጋ ካለፈው ዘጠነኛ ዙር ጋር ሲነጻጸር እስከ 20 በመቶ የዋጋ ጭማሪ እንዳሳየ ራሱ አስተዳደሩ የጠቀሰ ሲሆን፣ ይህንን ተከትሎም አንድ መኝታ ያለው ቤት በካሬ 3ሺ 438 ብር ሲከፈልበት፣

ለ48 ነጥብ 34 ካሬሜትር ቤት 166ሺ ብር ገደማ ይሸጣል። የ20 በመቶ ቅድመ ክፍያው ደግሞ 32ሺ 238 ብር ይሆናል።

ባለሁለት መኝታ ክፍል ኮንዶሚኒየም የ20 በመቶ ቅድመ ክፍያ ወደ 64ሺ ገደማ ሲሆን፣ ይህን ያህል ብር በአንድ ጊዜ ከፍሎ ከባንክ ጋር ለመዋዋልና ተጨማሪ የቤቱን ማጠናቀቂያ ወጪ ለማውጣት በወር ገቢ ለሚተዳደሩ

በርካታ ሰዎች አስቸጋሪ መሆኑን ዘጋቢያችን ያነጋገራቸው ቤት ፈላጊ ተናግረዋል ፡፡

አንድ ቤት ፈላጊ ባለአንድ መኝታ ኮንዶሚኒየም ቤት በዕጣ እንደደረሳቸውና በቅድሚያ የሚከፈለው የቤቱ ጠቅላላ ግምት 20 በመቶ ማለትም ወደ 32ሺ ብር ገንዘብ በአንዴ ለመክፈል መቸገራቸውን ተናግረዋል፡፡

ቀደም ሲል መንግስት የመኖሪያ ቤትን ችግር ለመቅረፍ በተመጣጣኝ ዋጋ በመስራት ዝቅተኛውን ሕብረተሰብ ጭምር የቤት ባለቤት አደርጋለሁ ብሎ ቃል ገብቶ እንደነበር ያስታወሱት አስተያየት ሰጪው፣ በአሁኑ ሰኣት

ግን ቤት ባለቤት መሆን የሚችለው 20 በመቶ ክፍያ ያጠናቀቀና ከባንክ ጋር መዋዋል የሚችል ብቻ ነው ብለዋል፡፡ በዚህ ምክንያት ብዙ ሰዎች ቤታቸውን ሳይረከቡ የሚቀሩ ሲሆን ፣ ብዙዎች ደግሞ ከአቅም በላይ ለሆነ ብድር በመዳረግ የኑሮ ቀውስ ውስጥ እየገቡ መሆኑን በመጠቆም ይህ ሁኔታ የግንባታውን ዓላማ የሳተ ነው ሲል ተችተውታል።


No comments:

Post a Comment