ጋሻው መርሻ .
ፈቃዱ የተባለ በአሁኑ ሰዓት ቂሊንጦ ታስሮ የሚገኝ የሰማያዊ ፓርቲ የአርባ ምንጭ አስተባባሪ የነበረ ወጣት ማዕከላዊ በተባለ ማጎሪያ ቤት ታስሮ በነበረበት ወቅት ራቁቱን እንዲቆም ይደረግ እንደነበር ተናግሯል፡፡ ‹‹ወንድ መርማሪዎች ፊት ለፊት ራቁቴን ስቆም ሀፍረት እንደሚሰማኝ የተረዱት መርማሪዎች ይድነቅህ ብለው ሴት መርማሪዎች ፊት ከ3 ሰዓት ላላነሰ ጊዜ እርቃኔን እንድቆም እገደድ ነበር›› ይላል ፈቃዱ በወቅቱ ስለነበረው ነገር ሲያስረዳ፡፡ እንደ ፈቃዱ ምስክርነት ከሆነ ሴት መርማርዎቹ ፈቃዱን ፊት ለፊታቸው አስቁመው ጌም ይጫዎታሉ፡፡ ይሳሳቃሉ፡፡ ‹‹እኔን ራቁቴን ከሶስት ሰዓት በላይ እስቁመው ደብድበው ይሸኙኛል›› ይላል የሕሊና እስረኛው ፈቃዱ፡፡
በተመሳሳይ ‹‹ልብሴን እንዳ
ወልቅ ከታዘዝኩ በኋላ ራቁቴን በወንድ መርማሪዎች ፊት ስፖርት እንድሰራ እገደድ ነበር›› ትላለች የዞን ዘጠኟ ማህሌት ፋንታሁን፡፡ ኤዶም ካሳዬም ተመሳሳይ ቶርቸር እንደተፈጸመባት ትናገራለች፡፡ መቸም ይህን ያክል በደል በወገኖቻቸው ላይ የሚፈጽሙ ሰዎች አንዳች ችግር ሳይኖርባቸው አይቀርም፡፡ ወንዶቹ ሴት አግብው ሴቶቹም ወንድ አግብተው ይኖራሉ፡፡ ወንድም ሆነ ሴት ልጆች አሏቸው፡፡ ታዲያ እንዴት ሴት ልጅ አቅፎ የሚያድር ገላ በሴት እህቶቻችን ላይ እንዲህ አይነት ብልግና ለመፈጸም ምን አስጨከናቸው? ወንድ ልጅ ደረት ላይ ተለጥፋ የምታድር ሴትስ ብትሆን እንዲህ አይነት ለአዕምሮ የሚከብድ ነገር ለማድረግ ጭካኔውን ከየት ተማረችው? ሀገራችንስ ወዴት እያመራች ነው? በእውነት እንደ ዜጋ ያሳዝናል፡፡ እንደ ሀገር ሲያስቡት ደግሞ ያሸማቅቃል፡፡ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ሴትን ልጅ እርቃኗን አስቁሞ ከመመርመር የወረደ ነገር ምን አለ፡፡ እንደ ሀገር ምን አይነት የሞራል ዝቅጠት ውስጥ እንደገባን አይነተኛ ማሳያ መስሎ ይሰማኛል፡፡
የተከበረውን የሰው ልጅ ገላ እርቃን እንዲሆን አድርጎ መደሰት ምንድን ነው ትርፉ? ቂም በቀልን ለልጅ ልጆቻችን ከማውረስ በቀር፡፡ እነዚህ ልጆች ለሀገራቸው ነግ ተጨንቀው፤ የመንግስት ዝርክርክ አሰራሮችን ለማስተካከል በልጅ አዕምሯቸው የመሰላቸውን ነገር ስለጻፉ፤ ስህተት ነው ብለው ያሰቡትን ነገር ስለተቹ ይህን ሁሉ ግፍ በአካላቸው ላይ መፈጸም ምን አመጣው፡፡
እኛ ውጭ ያለነው እስረኞችስ ብንሆን ይህን ነገር ለማቆም ምን አደረግን ብዬ ስጠይቅ ምንም የሚል መልስ አገኛለሁ፡፡ በቃ ቁመን ስንጠብቅ የእኛም ተራ ይደርስና እርቃናችን እንድንቆም ይደረጋል፡፡ ያኔ እንደ አዲስ ነገር ይወራል መልሶ በሳምንቱ ይረሳል፡፡ ይህ የክፋት አዙሪት እንዲቆም የበኩላችን አስተዋጽኦ ማድረግ የግድ ይኖርብናል፡፡ ያለ በለዚያ ግን አዙሪቱ እኛ ጋር መድረሱ አይቀርም፡፡
No comments:
Post a Comment