ሀገራችን ኢትዮዽያ የተለያዩ ቋንቋዎች ፣ የተለያዩ ባህሎችና የተለያዩ እምነቶች ያሉባት ሀገር እንደመሆኗ መጠን እነዚህ ባህሎቿ፣ ቋንቋዎቿ እና እምነቶችዋ ያለመታደል ሆኖ በእኩልነት ተከብረው የማያውቁባት ሀገር ሆና ቀጥላለች። የዘረኝነት መንስኤው ዝርዝሩ ብዙ ቢሆንም ዋነኛው ግን ኋላ ቀር የሆነው የሀገራችን ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፓለቲካዊ ሁኔታ ነው። ምንጩ ድህነትን ማሸነፍ፣ ፍትህ ማስፈን፣ መብቶች ማስከበር ያልቻለ ያልተሟላ የሀገርና የመንግስት ግንባታ ድክመት ነው። ዛሬም ወደኋላ እየተመለስን በታሪክ የተካሄድ ጦርነቶችንና ወረራዎችን እያነሳን የምንካሰሰው እነሱን ምክንያት እያደረግን የዘር ፖለቲካ ለመቀስቀስ የተመቸን ሌሎች እንደ ኢትዮዽያ በጦርነትና በወረራ የተፈጠሩ ሀገሮች መገንባት የቻሉትን የበለፀገ የዜጎች መብቶች የተከበሩበት ሀገር መገንባት ባለመቻላችን ነው። ብልጽግና፣ እድገትና የዜጎች መብት በእኩልነት መከበር እንዴት ማህበራዊ መግባባትን፣ መቻቻልን፣ ሀገራዊ የሆነ አንድነትን መፍጠር እንደሚችል በአለማችን ብዙ ሀገሮችን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል።
ዜጎች በአንድ ሀገር ዜግነታቸው ሳይሆን በመንደራቸው በቀያቸው በጎጣቸው በዘራቸው እንዲሰባሰብና እንዲያስቡ የሚያደርገው መሰረታዊ ሁኔታ ከኢትዮዽያ የፓለቲካ፣ የማህበራዊና የኢኮኖሚ እውነታ ድርና ማግ ነው።
መሰረታዊ በሆነ መንገድ ዘረኝነትና ዘር ላይ የቆመ ፓለቲካዊ መሰባሰብን በሀገራችን ለማስወገድ ሀገራችንን በከፍተኛ ደረጃ በኢኮኖሚ ማሳደግ የዜጎች መብት የሚያስከብር ፓለቲካዊ ሁኔታ መፍጠር ይጠይቃል። ዛሬ ሀገራችን ባለችበትና ዘረኛነት ከመቼውም በላይ በሚራገብበት ሁኔታ እንዴት ብልጽግናን ማምጣት፣ እንዴትስ የዜጎችን መብት በእኩልነት የሚያስከብር የስርአት ግንባታ ሂደት ማስጀመር ይቻላል? ይህ ጥያቄ ኢትዮዽያን በዜጎቿ የዴሞክራሲ የነፃነት የፍትህና እኩልነት መብቶች ዙሪያ የበለጸገችና የታፈረች፣ እንዲሁም አንድነቷ የጠበቀ ሀገር ለመፍጠር ህልም ላላቸው የፓለቲካ ድርጅቶች ትልቁ ፈተና ነው።
በሀገራችን የዘረኝነት መንስኤዎች ከላይ እንደተገለጸው ከኋላቀርነታችን ጋር የተያያዙ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፓለቲካዊ ጉዳዮች ይሁኑ እንጂ ይህን ሁኔታ በመጠቀም ዘረኛነት በኢትዮዽያ ሊፈጥር ከሚችለው ፈተና በላይ አደገኛ እንዲሆን ያደረጉት አካላት አሉ። የኢትዮዽያችን አሳዛኝና እጅግ አሳሳቢ ሁኔታ የመነጨው የሀገሪቱና የሕዝቧ ህልውና ከፍተኛ አደጋ ላይ የወደቀው፣ የብልጽግናና የመረጋጋት የመቻቻል ፈተናዎች የሆነውን የዘረኛነት መርዝ በስልጣን ላይ የሚገኘው የአገዛዙ የፓሊሲ ምሶሶ አድርጎ የሚተገብረው መሆኑ ነው። ትልቁ የሀገሪቱ ችግርና አደጋ ዘረኛ የሆኑ ቡድኖችን የሚፈለፍል ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እውነታ በሀገሪቱ መገኘቱ መሆኑ እየታወቀ በመንግስት ደረጃ ዘረኛነትን የሚያስፋፋና የሚያጠናክር ድርጅት ስልጣን የያዘበት ሀገር ሆናለች አገራችን ኢትዮዽያ።ሌላው መካድ የሌለበት የሀገራችን እውነታ የገዢውን ፓርቲ ዘረኛ እምነት የሚጋሩ ከገዢው ፓርቲ የማይተናነሱ የዘረኛ ፓሊሲዎች የሚያራምድ አካላት በኢትዮዽያዊ ውስጥ መኖራቸውን ነው። ገዢውን ፓርቲ ከሚቃወሙ ኃይሎች መካከል ሳይቀር ዜጎችን በደምና በአጥንታቸው ጥራት እየመዘኑ የዘር የፓለቲካ ድርጅት ያቆሙ አካላት ያሉበት ሀገር ነው።
በዘር ላይ የተመሰረተ ድርጅት ማቆም ከኢህአዴግ በፊትም የነበረ ነው። ኢህአዴግ ቢወገድም ከኢህአዴግ ጋር የሚቀበር ጉዳይ አይደለም። ሆንም ግን ከማንኛውም አካል በላይ ኢህአዴግ በስልጣን መቀጠል ከዘረኛነት ጋር የተያያዘውን አደጋ የከፋ ያደርገዋል። የከፋ የሚሆንበት ምክንያት ገዢው ፓርቲ የሚያራምደው ፓሊሲ ህዝብ በዘር ላይ ተከፋፍሎ እርስ በርሱ እንዲጠራጠርና እንዲተላለቅ በማድረግ የራሱን የስልጣን ዘመን ያራዝምበታል። የዛሬን እዚህ ላይ ላብቃና በሚቀጥለው ጽሁፌ ላይ ዘረኝነት በተለይ ሴቶች ላይ የሚያስከትለው አደጋ፣ የሴቶችስ ተሳትፎ ዘረኝነት ላይ ምን መምሰል አለበት የሚሉ እና ሌሎች ይህንን ነቀርሳ የሆነ በሽታ እንዴት ከሀገራችን ላይ ማስወገድ እንደምንችል ሊረድ የሚችሉ የመፍትሄ እይታዎቼን አካፍላችሀለው። ቸር እንሰንብት።
ደጅይጥኑ ጥላሁን
No comments:
Post a Comment