ራኒያ ባደዊ በቃለምልልስ ወቅት አምባሳደር ማህሙድ ድሪር ላይ ስልክ በማቋረጣ ከስራ መታገዷ የሚታወስ ነው።
ጋዜጠኛዋ ከአምባሳደር ጋር ያረገችው ቃለ ምልልስ በ አማርኛ እንደሚከተለው አዘጋጅተናል።
አምባሳደር ማህሙድ ድሪር ከጋዜጠኛዋ ጋር አድርገውት በነበረው ቃለ ምልልስ ኢትዮጵያ የግድቡን ግንባታ እንደምትቀጥልና የግድቡ ግንባታ በግብጽና ሱዳን ላይ የሚያሳድረው አንዳችም ጎጂ ተጽእኖ እንደሌለው የባለሙያዎች ቡድን ማረጋገጡን አስረድተዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ አምባሳደር ማህሙድ ጋዜጠኛዋን በአነጋገሯ ላይ የሚታየውን ዝቅ አድርጎ የማየትና የንቀት አነጋገር እንድታስወግድ ነግረዋታል፡፡ ጋዜጠኛዋ ከአምባሳደር ማህሙድ ድሪር ጋር አድርጋው የነበረው ቆይታ የሚከተለውን ይመስል ነበር…፡፡
ጋዜጠኛዋ፡- የተከበሩ አምባሳደር እንዴት አመሹ ?
አምባሳደር ማህሙድ ድሪር፡- እንደምን አመሸሽ፡፡ በመጀመሪያ ሚንስትሩን ለአዲሱ የሥልጣን ቦታዎ በመብቃትዎ እንኳን ደስ ያሎት እላለሁ፡፡ በሚንስትር መስሪያ ቤቱና በኢትዮጵያ መካከል የተለመደው መልካም ግንኙነት ይቀጥላል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከበርካታ የግብጽ የሚንስትር መሥሪያ ቤቶች ጋር ተባብረን እየሰራን ነው፡፡
ጋዜጠኛዋ፡- በጣም ጥሩ፡፡ ይህ ማለት ሁለቱም ልዩነታቸውን አቻችለው ግማሽ መንገድ በመጓዝ መተባበር ይችላሉ ማለት ነው ?
አምባሳደር ማህሙድ ድሪር፡- በመጀመሪያ ደረጃ…ከሚንስትሩ ጋር ስታወሪ በነበረበት በተደጋገመ ፖለቲካዊ ቃና ነው እያወራሽ ያለሽው፡፡ እኛ ግን አሁን [አቋረጠችው]
ጋዜጠኛዋ፡- የትኛው…በምን መልኩ፡፡ እስኪ ግለጽልኝ፡፡
አምባሳደር ማህሙድ ድሪር፡- ማየት ያለብን አጠቃላዩን የኢትዮ-ግብጽን ግንኙነት እንጂ ጉዳዩን ከህዳሴው ግድብ ጋር ብቻ አያይዞ ማየት ተገቢ አይደለም፡፡ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ከዚያም በላይ የላቀ ጉዳይ ነው፡፡ ግድቡ የግብጻውያንን ሕይወት አደጋ ላይ ይጥላል የሚለው ሀሳብ በሁለቱ ሀገራት ድርድር ውስጥ ቦታ የለውም፡፡ እኛ አሁን የደረስንበት…[አቋረጠችው]
ጋዜጠኛዋ፡- እና…የግብጻውያንን ሕይወት አደጋ ላይ የማይጥል ከሆነ ለምንድነው ግብጽ ልዑካኖቿን ወደ ኢትዮጵያ የምትልከው፡፡
አምባሳደር ማህሙድ ድሪር፡- ይቅርታ…እባክሽን መጀመሪያ እንድጨርስ ፍቀጅልኝ፡፡
ጋዜጠኛዋ፡- ቀጥል፡፡
አምባሳደር ማህሙድ ድሪር፡- ይሄን ግድብ እንገነባለን፡፡ እናም እንቀጥልበታለን፡፡ ግብጽና ሱዳንንም አይጎዳም፡፡
ጋዜጠኛዋ፡- ህምምም [በማሾፍ]…እሺ የተከበሩ አምባሳደር…እንደገና የእኔ ጥያቄ…እናንተ ኢትዮጵያውያን ይሄ ግድብ ግብጽ ላይ ችግር አይፈጥርም የምትሉ ከሆነ…እና ለምንድነው ይሄ ሁሉ የኮሚቴ መሰብሰብና ኢትዮጵያ ሄዶ መደራደር ያስፈለገው፡፡ የግብጽ መንግሥት ነገሩ አልገባውም ማለት ነው…? እናም ጊዜውን እያባከነ…እና ምንድነው ነገሩ…፡፡
አምባሳደር ማህሙድ ድሪር፡- አይደለም…አይደለም፡፡ በአንጻሩ ነገሩን በጨለምተኝነት እያየሽው ነው፡፡ እስካሁን የደረስንበት ሁሉ በጎ ነው፡፡ በመጀመሪያ በኢትዮጵያ አነሳሽነት፣ አለማቀፍ ባለሙያዎችን ጨምሮ ከኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን የተውጣጡ ባለሙያዎች ያሉበት የባለሙያዎች ቡድን ተቋቋመ፡፡ ቡድኑም ግድቡ ግብጽንና ሱዳንን እንደማይጎዳና ዓለማቀፍ መስፈርቶችን እንደሚያሟላ ገለጸ፡፡ ሌላው ደግሞ ስለግድቡ ስናወራ ድህነትን ስለመዋጋት እያወራን ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ስለግድቡ ስናወራ ከኢንዱስትሪ መስፋፋት ጋር ተያይዞ አካባቢውን ስለሚያሰጋው የኃይል አቅርቦት እያወራን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በግብርና ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ኢንዱስትሪ ለማስፋፋት ከውኃ ሀይል ኤሌክትሪክ ከማመንጨት የተሻለ ከአካባቢ ጋር ተስማሚ የሆነ ስልት የለም፡፡
ጋዜጠኛዋ፡- እሺ…እሺ የተከበሩ…ግብጽ በተደጋጋሚ ልማትን ወይም የኢትዮጵያውያን ኑሮ መሻሻልን እንደማትቃወም ገልጻለች፡፡ ግብጽ ልማትን ትደግፋለች፡፡ እናም የመስኖ ሚንስትሩ እንዳሉት ግብጽ ግድቡ ላይ የተወሰነ ስልጣን እንዲኖራት ትፈልጋለች፡፡ እናም በግድቡ ቴክኒካል አስተዳደር ላይ መሳተፍ እንፈልጋለን፡፡ ግብጽ በሁሉም ጉዳይ ላይ ትስማማለች፡፡ ከዚያ በፊት ግን ግድቡ ወደ በፊቱ ሁኔታ እና መጠን ይመለስ…ያም ማለት አሁን ያለበት 47 ቢሊየን በሰዓት ሳይሆን…[አምባሳደር ማህሙድ አቋረጧት]
አምባሳደር ማህሙድ ድሪር፡- ይቅርታ…ይቅርታ፡፡ ይሄን ነገር እኮ አልፈነዋል፡፡ ይሄ አሁን የሚመለከተን ጉዳይ አይደለም፡፡ አሁን የሚመለከተን [አቋረጠቻቸው]
ጋዜጠኛዋ፡- አልፈነዋል ስትል ምን ማለት ፈልገህ ነው፡፡ ይህ ማለት አንቀበለውም ማለትህ ነው ወይንስ፡፡
አምባሳደር ማህሙድ ድሪር፡- የሚመለከተን የባለሙያዎቹ ቡድን ያቀረበውን ምክረ ሀሳብ መተግበር ነው፡፡ እናም ይቅርታ አድርጊልኝና ግብጽ ግድቡ ላይ ይኑረኝ ያለችውን የማስተዳደር ድርሻም በተመለከተ ይሄን የመወሰን ስልጣን የኢትዮጵያ እንጂ የግብጽ አይደለም፡፡
ጋዜጠኛዋ፡- አሃ…ይሄ ማለት ግድቡን በጋራ እንድናስተዳድረው አትፈልጉም ማለት ነው…፡፡
አምባሳደር ማህሙድ ድሪር፡- ነገርኩሽ…ይሄ የኢትዮጵያ ውሳኔ ነው፡፡
ጋዜጠኛዋ፡- እንደገና ልጠይቅህ፡፡ እንደሚገባኝ አሁንም አሁን ባለው የግድቡ መጠን ላይ ሙጭጭ ብላችኋል፡፡
አምባሳደር ማህሙድ ድሪር፡- ስለግድቡ ምንም የምታውቂ አይመስለኝም እናም ደግሞ በንቀት ስሜት ነው የምትናገሪው፡፡ ይሄ ደግሞ በሁለቱ ሀገራት መካከል ላለው ንግግር አንዳችም የሚጨምረው ነገር የለም፣ ማንንም አይጠቅምም [አቋረጠቻቸው]
ጋዜጠኛዋ፡- ሚስተር አምባሳደር…መጠንዎን ያለፉ ይመስለኛል፡፡ የእኔን ቃላት ማረም የእርስዎ መብት አይመሰለኝም፡፡ እኔም የእርስዎን ቃላት አላረምክዎትም፡፡ የግብጽ ህዝብ የሚያገባውን ጉዳይ አስመልክቼ መጠየቅ መብቴ ነው፡፡ የተራቀቁ ጥያቄዎች አይደሉም፡፡ መጠየቅ መብቴ ነው ሚስተር አምባሳደር፡፡ እናም ስጠይቅ ወይ መመለስ አለበለዚያም መልስ መስጠት አልፈልግም ማለት፡፡ ጠየቅኩህ - እናም ወይ መልስ አልያም መልስ መስጠት አልፈልግም በል - ያንተ መብት ነው፡፡ ከዚህ ውጪ መብት የለህም፡፡ የተከበሩ…ከመጠንህ አልፈሀል፡፡ እናም አመሰግንሀለሁ፡፡ በጣም አመሰግንሀለሁ፡፡
ወዲያውኑ ጋዜጠኛዋ አምባሳደሩ የሚሉትን ሳትሰማ ስልኩን ጆሯቸው ላይ ዘግታዋለች፡፡ በዚህ መሃል ስልኩ ከመዘጋቱ በፊት አምባሳደር ማህሙድ “አይደለም…ይልቁንም አንቺ ራስሽ እንደጋዜጠኛ ወሰንሽን አልፈሻል” ሲሉ ተሰምቷል፡፡
No comments:
Post a Comment