Thursday, June 22, 2017

የአቶ አለምነው መኮንን የግል አጃቢ በሆቴል ውስጥ መገደላቸው ታወቀ

የአማራ ክልል ከፍተኛ ባለስልጣንና የብአዴን ፅ/ቤት ሃላፊ የአቶ ዓለምነው መኮንን የግል አጃቢ ሆቴል ውስጥ መገደላቸው ታወቀ። በሌላ ሰው ሥም በተያዘ ሆቴል ውስጥ አጃቢው መገደላቸውና ሆቴሉን የያዘው ሰው አለመታወቁ አነጋጋሪ ሆኗል። ግድያውንም ተከትሎ በብአዴን አመራር በተለይም በአቶ ዓለምነው መኮንን ዘንድ ሥጋት መፈጠሩ ተመልክቷል።
የኣቶ ዓለምነው መኮንን አጃቢ አቶ አንዋር መሐመድ የተገደለው ሰኞ ሰኔ 12/ 2009 በባህርዳር ቀበሌ 04 በሚገኘው ግሪንላንድ ሆቴል ሲሆን ይህ ሆቴል በብአዴን ባለስልጣናት የሚዘወተር መሆኑም ታውቋል። ይህ ሆቴል ከዚህ ቀደም የቦንብ ጥቃት እንደተፈፀመበትም ማስታወስ ተችሏል። 
ግድያው በዋናነት የተነጣጠርው በአቶ ዓለምንው መኮንን ላይ እንደነበር የሚገልፁት ምንጮች አጃቢያቸው ተባባሪ ሆኖ ባለመገኘቱ ሣይገደል እንዳልቀረ አመልክተዋል። ሟች ከአቶ ዓለምነህ ጋር የአንድ አካባቢ ሰዎች እንደሆኑም መረዳት ተችሏል። ከግድያው ጋር ተያይዞ የአማራ ክልል ወንጀል መከላከል ሃላፊ ኮማንደር አሠፋ ስንታየሁ ሥራቸውን መልቀቃቸውም ታውቋል።

ግድያውን ተከትሎ ማክሰኞ ዕለት በክልሉ የሚገኙ ደህንነቶች ስብሰባ የተቀመጡ ሲሆን፣ የክልሉ የወንጀል መከላከል ኃላፊ ኮማንደር አሰፋ ስንታየሁ “ በዚህ ሁኔታ መሥራት አልችልም” በማለት ስራውን በፈቃደኝነት ለቋል። የኮማንደሩ ከኃላፊነቱ መልቀቅ ተጨማሪ ስጋት ማሳደሩን ምንጮች ለኢሳት ገልጸዋል።
ማክሰኞ በነበረው ግምገማ ላይ የክልሉ የጸጥታ ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባለሸ መሄዱ፣ በክልሉ ያለውን የትጥቅ ትግል መቆጣጠር አለመቻሉ፣ ለመረጃ ከፍተኛ ገንዘብ እየወጣ መረጃ መጥፋቱ ተነግሯል።
በዚህ ግምገማ በፖሊስ ኮሚሽን ላይ ወደፊት ጥቃት እንደማይፈጸም እርግጠኛ መሆን እንደማይቻል ከመድረኩ የተገለጸ ሲሆን፣ ግምገማው ወደ እርሱ ማነጣጠሩን የተረዳው ኮማንደር አሰፋ “ ዛሬ ላይ ማን ለማን እንደሚሰራ አይታወቅም” የሚሉና ሌሎችንም ጠንካራ የተባሉ ትችቶችን በመሰንዘር ፣ በገዛ ፈቃዱ ስልጣኑን መልቀቁንና በስራው የመቀጠል ፍላጎት እንደሌለው ተናግሯል።
እንደውስጥ ምንጮች ገለጻ የብአዴን ባለስልጣናት ከህወሃት ጋር በሚኖራቸው ግንኙነት ዙሪያ ከሁለት ተከፍለዋል።
አብዛኞቹ የክልሉ ፖሊሶችና ወታደሮች ብአዴን ራሱን ከህወሃት ተጽእኖ አላቅቆ የክልሉን ህዝብ መብትና ማንነት እንዲያስከብር ይፈልጋሉ። የደህንነትና የጸጥታ አባላቱ እንዲሁ በክልሉ ከተሰማራው ኮማንድ ፖስት ጋር ያላቸው ግንኙነት በጣም የተዳከመ ነው። ይህ ጉዳይ በፌደራል ደረጃ የተቀመጡ የህወሃት ባለስልጣናትን እያሣሰበ መምጣቱን ተከትሎ፣ በቅርቡ ሹም ሽር እንዲካሄድ ቢደረግም ነገሮች እየባሱ እንጂ እየተሻሻሉ አለመምጣታቸው ታውቋል።

No comments:

Post a Comment