ኢሳት (ሰኔ 6 ፥ 2009)
የባህርዳርና የኮምቦልቻ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎች ለብአዴኑ ጥረት ድርጅት መተላለፋቸውን የኢሳት ምንጮች ገለጹ።
የባህርዳር ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ በጣሊያን ወረራ ምክንያት ለደረሰ ጉዳት በደም ካሳነት ለህዝብ ሲባል የተሰራ እንደነበር ይገለጻል።
በቅርቡ 5 መቶ ሚሊዮን ወጪ ተደርጎ ማስፋፊያ የተሰራለትን የባህርዳር ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ እና የኮምቦልቻውን ጨምሮ ጥረት መጠኑ ባልታወቀ ርካሽ ዋጋ እንደተረከበው ለማወቅ ተችሏል።
በአማራ ክልል ከዳሸን ቢራ ፋብሪካ ውጪ የረባ ነገር አልሰራም የሚባለው ጥረት ሁለቱን ነባር ፋብሪካዎች ገዝቶ ከኤፈርት ጋር በዕኩል ደረጃ ለመታየት የሚያደርገው ጥረት ነው በማለት ህብረተሰቡ እየተቃወመ መሆኑን ምንጮች ገልጸዋል።
በብአዴኑ አቶ ታደሰ ካሳ (ጥንቅሹ) ቦርድ ሰብሳቢነት የሚመራው ጥረት በቅርቡ በዳሸን ቢራ ላይ በተደረገው የህዝብ ተቃውሞ የኢኮኖሚ ኪሳራ እንደደረሰበት ይታወቃል።
ዳሸን ቢራ ምርቱን ወደ ትግራይ በመውሰድ ለመሸጥ ቢሞክርም አሁንም ከኪሳራ እንዳልወጣና ችግር ውስጥ መሆኑ ይነገራል።
ጥረት በአማራ ክልል በርካታ የልማት ፕሮግራሞችን በመቅረፅ ብዙ የመሰረት ድንጋዮችን ሲያስቀምጥ ከመኖር ያለፈ ስራ ባለመስራቱ በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት የሌለው ድርጅት እንደሆነ ታዛቢዎች ይገልጻሉ።
አሁን ደግሞ የህዝብ ንብረት የሆኑት የባህር ዳር እና የኮምቦልቻ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች ወደራሱ በመጠቅለል ገዝቼዋለሁ ማለቱ በህዝብ ዘንድ ቁጣን እየቀሰቀሰ መሆኑን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
No comments:
Post a Comment