(ኢሳት ዲሲ–ሕዳር 24/2011) በቤንሻንጉል ጉምዝና ኦሮሚያ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ጥቃት በመፈጸም ላይ ያለው የኦነግ ጦር መሆኑን የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል አስታወቀ።
ለእርዳታ የተዘጋጀ ከ2ሚሊዮን ብር በላይ በታጣቂዎች መዘረፉም ታውቋል።
በሁለቱ ክልሎች መካከል የተፈጠረው ውጥረት ቀጥሏል።
መከላከያ ሰራዊትና የፌደራል ፖሊስ በግጭቱ አካባቢዎች መስፈራቸውን የቤንሻንጉል ጉምዝ ፖሊስ ኮሚሽነር አቶ ሰይፈዲን ሀሩን ለኢሳት ገልጸዋል።
ለውጡን ለማደናቀፍና ኦሮሚያ ክልልን የጦርነት ዓውድማ የማድረግ ዕቅድ መኖሩን የኦሮሞ ዴምክራሲዊ ፓርቲ ኦዴፓ አስታውቋል።
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር በበኩል ለኦዴፓ ማሳሰቢያ ሰጥቷል። ውጪያዊ ምክንያት መደርደር ይቁምና የክልሉን ደህንነት ማስጠበቅ ይቅደም ብሏል ኦነግ።
ሶስተኛ ወሩን እያጠናቀቀ ነው። ካማሼ ላይ የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል የጸጥታ ሃላፊዎች ስብሰባ ተቀምጠው ሲመለሱ መንገድ ላይ በተፈጸመባቸው ጥቃት መገደላቸውን ተከትሎ የተቀሰቀሰው ግጭት ከ100ሺህ በላይ ሰዎችን አፈናቅሎና ከ100 በላይ ሰዎችን ለህልፈት ዳርጎ በአዲስ የግጭት መስመር ላይ ወጥቷል።
ከሰሞኑ እንደአዲስ በተቀሰቀሰ ግጭት ብቻ አርባ ሰዎች መገደላቸው ታውቋል።
ያን ጊዜ ጀምሮ በሁለቱ ክልሎች መካከል ባሉ አካባቢዎች መፈናቀሉና ግድያው ሳይቋረጥ ቀጥሏል።
ባለፈው ሳምንት በርካታ የኦሮሚያ ክልል ፖሊሶች መገደላቸው ጉዳዩን አሳሳቢ አድርጎታል።
በቤንሻንጉል ጉምዝ የሚንቀሳቀሱና ለዘመናት የህዝቡን ሰላም ሲነሱ ነበሩ የተባሉ ሃይሎች ለጥቃት የሚጠቀሙት የጦር መሳሪያ ቀስት መሆኑን የሚገልጹት ምንጮች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በተደራጀና ዘመናዊ በሆነ የጦር መሳሪያ ጥቃት የሚፈጸም በመሆኑ በመንግስት በኩል በልዩ ትኩረት ክትትል እየተደረገበት እንደሚገኝ ነው የደረሰን መረጃ የሚያመለክተው።
ባለፈው ሳምንት በኦሮሚያ ፖሊሶች ላይ የተፈጸመው ግድያ በአካባቢው የሚንቀሳቀስ የተደራጀ ሃይል ለመኖሩ አመላካች ሆኗል።
የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል መንግስት ከአንድ ወር በፊት በክልሉ ማሰልጠኛ ከፍቶ ወታደራዊ እንቅስቃሴ ሲደረግ ደረስኩበት ብሎ ርምጃ መወሰዱን አስታውቆ ነበር።
በወቅቱም የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ታጣቂዎች እንደሚንቀሳቀሱ የጠቀሰው የክልሉ መንግስት በይፋ ኦነግን ተጠያቂ ማድረጉ ይታወሳል።
ኢሳት ያነጋገራቸው የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር አቶ ሰይፈዲን ሀሩን ይህንኑ ክስ ያጠናክሩታል። ከኦነግ ያፈነገጠ ሃይል ጥቃቱን እየፈጸመ ነው ሲሉ ከካማሼው ጥቃት ጀምረው ይገልጻሉ።
ምንም እንኳን የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ኦዴፓ በስም ጠቅሶ ለቀውሱ ተጠያቂ ያደረገው አካል ባይኖርም በለውጡ ያኮረፉ ሃይሎች የሚፈጽሙት አሰቃቂ ድርጊት ሲል አውግዞታል።
ለውጡን ለማደናቀፍና የኦሮሚያ ክልልን የጦርነት አውድማ የማድረግ ዕቅድ አለ ሲል ነው ኦዴፓ የገለጸው።
ኦዴፓ ይህንን እቅድ ለማክሸፍ በሙሉ ሃይሉ መንቀሳቀስ መጀምሩንም አስታውቋል።
የገቡበት ጉድጓድ ገብተን ለፍርድ እናቀርባቸዋለን ሲልም አስጠንቅቋል። የኦሮሞ ነጻነት ግንባር በሰጠው ምላሽም ኦዴፓ ላይ አነጣጥሯል።
ውጪያዊ ምክንያት ከመስጠት የክልሉን ደህንነት ማስከበሩ ላይ ኦዴፓ ስራ መስራት አለበት ነው ያለው ኦነግ።
የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር አቶ ሰይፈዲን ሀሩን ለኢሳት እንደገለጹት አሁንም አካባቢው ቀውስ ላይ ነው።
ለእርዳታ እየተላከ ያለን ከ2ሚሊዮን ብር በላይ በእነዚሁ ታጣቂዎች መዘረፉን ገልጸዋል። በአዋሳኝ አካባቢዎቹ ሰላማዊው ህዝብ እንቅስቃሴው ተገድቧልም ይላሉ።
ካለፈው ሳምንት መጨረሻ አንስቶ በአዋሳኝ አከባቢዎቹ የመከላከያ ሰራዊት መሰማራቱን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር አቶ ሰይፈዲንም የመከላከያ ሰራዊት መግባቱን ያረጋገጡ ሲሆን የተሻለ ሁኔታ ይፈጠራል ብለን እንጠብቃለን ብለዋል።
ዘግይተው በሚወጡ መረጃዎችም መከላከያ ሰራዊት በአንዳንድ የምስራቅ ወለጋ ከተሞች ገብቷል።
በዚህ ጉዳይ ላይ ከኦዴፓም ሆነ ከኦነግ አስተያየት ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም።
No comments:
Post a Comment