Friday, December 14, 2018

በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን ሞያሌ ከተማ በተከሰተ ግጭት እስካሁን የ13 ሰዎች ሕይወት ማለፉ ተነገረ፡፡

በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን ሞያሌ ከተማ በተከሰተ ግጭት እስካሁን የ13 ሰዎች ሕይወት ማለፉ ተነገረ፡፡ ከአንድ መቶ የሚበልጡ ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል ተብሏል፡፡ የኦሮሚያ ክልል ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊ አቶ አድማሡ ዳምጠው ዛሬ ለሸገር እንደተናገሩት ከትናንት በስትያ አንስቶ በቦረና ዞን ሞያሌ ከተማ ግጭት ተከስቷል፡፡ በግጭቱ እስከ አሁን የ13 ሰዎች ህይወት ማለፉ የተነገረ ሲሆን ከአንድ መቶ የሚበልጡ ደግሞ ቆሰለዋል ተብሏል፡፡ በንብረት ላይም ጉዳት መድረሱን አቶ አድማሱ ተናግረዋል፡፡


የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ የቦረና ዞን ያቤሎ ከተማ እና ሌሎች ወረዳዎች ነዋሪዎች መንግስት የህግ የበላይነትን ያስከብርልን፤ ግድያ ይቁም በሚል ሠላማዊ ሠልፍ ማካሄዳቸውን አቶ አድማሡ ነግረውናል፡፡ ግጭቱ እንዲቆም የኦሮሚያ ክልል መንግስት ከፀጥታ ሃይሎች ጋር በመሆን እርምጃ መውሰድ ጀምሯል ያሉት አቶ አድማሡ ለተጎዱ ዜጎችም ድጋፍ እየተደረገ እንደሚገኝ ነግረውናል፡፡

ህዝቡ ግድያ ይቁም በሚል እያነሳ ያለውን ጥያቄ መንግስት እንደሚያከበር የተናገሩት የቢሮ ሃላፊው የግጭት መንስዔዎችን በመለየት ለዘላቂ መፍትሄው ይሰራልም ብለዋል፡፡ ህብረተሰቡም አጥፊዎችን በማጋለጥ እና ግጭቶች በዘላቂነት እንዲቆሙ መንግስት ለጀመረው ጥረት ድጋፍ በመስጠት ዕገዛ እንዲያደርግ አቶ አድማሡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በተጨማሪም በሞያሌ ሆስፒታል የሚሠሩ የጤና ባለሞያዎች አካባቢውን ለቀው ያቤሎ እንደሚገኙና የተጎዱ ወገኖች ርዳታ በ ያቤሎ ሆስፒታል እየተሠጠ መሆኑን ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል ።

No comments:

Post a Comment