ኢሳት (የካቲት 29 ፥ 2009)
አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ በተለያዩ የሃገሪቱ ክልሎች የተከሰተን የምግብ ዋጋ ንረት ተከትሎ የሃገሪቱ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት በየካቲት ወር በአንድ በመቶ በማደግ ሰባት በመቶ ሆኖ መመዝገቡን የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ገለጸ።
በየካቲት ወር ምግብ ነክ የዋጋ ግሽበት 7.8 በመቶ ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን፣ ቁጥሩ ካለፈው ወር የ2.8 በመቶ አካባቢ ጭማሪ ማሳየትን ሮይተርስ የኤጀንሲውን ሪፖርት ዋቢ በማድረግ ማክሰኞ ዘግቧል።
በሃገሪቱ ተከስቶ ያለው የድርቅ አደጋ የምግብ ዋጋ በከፍተኛ እንዲጨምር ማድረጉንና የኢትዮጵያ የዋጋ ግሽበት ከፍ እንዲል አስተዋጽዖ ማድረጉ ተመልክቷል።
የዋጋ ግሽበቱ እየጨመረ መምጣት በኢኮኖሚ እድገቱ ላይ ከሚያሳድረው ተጽዕኖ በተጨማሪ የብር የመግዛት አቅም እያሽቆለቆለ እንዲሄድ ማደረጉን የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ይገልጻሉ። የኢትዮጵያ የውጭ ንግድ እየቀነሰ መምጣት ከዋጋ ግሽበቱ በተጨማሪ በሃገሪቱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይም ጫና ማሳደሩ ተነግሯል።
ይኸው የዋጋ ግሽበት ማሻቀብና የኢኮኖሚ ሁኔታው አለመረጋጋት ይገኛል ተብሎ በተገመተው ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ላይ ማነቆ ሊሆን እንደሚችል የአለም ባንክን ጨምሮ የተለያዩ የፋይናንስ ተቋማት ሲያሳስቡ መቆየታቸው ይታወሳል።
አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች የሚኖሩ ነዋሪዎች በመሰረታዊ የምግብ ፍላጎቶች ላይ ከፍተኛ እጥረትና የዋጋ ንረት በማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ችግር እየፈጠረ መሆኑን አስታውቀዋል።
No comments:
Post a Comment