Monday, March 20, 2017

በተለምዶ “ቆሼ” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የተቀበሩ ሰዎችን ለማግኘት ወራትን ሊፈጅ ይችላል ተባለ

ኢሳት (መጋቢት 11 ፥ 2009)
በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ “ቆሼ” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በደረሰው አደጋ በቆሻሻ ክምር የተቀበሩ ሰዎችን ሙሉ ለሙሉ ለማግኘት ወራትን ሊፈጅ እንደሚችል የነብስ አድን ሰራተኞች አስታወቁ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍለጋን የማካሄዱ ዘመቻው ወደ መጠናቀቁ ተቃርቧል ቢልም፣ የአካባቢው ነዋሪዎች አሁንም ድረስ ከ80 የሚበልጡ ሰዎች አለመገኘታቸውን ገልጸዋል። የነብስ አድን ሰራተኞች በበኩላቸው በቆሻሻ ክምሩ ያልተገኙ ሰዎችን ሙሉ ለሙሉ ፈልጎ ለማግኘት የወራት ጊዜን እንደሚወስድ ለሮይተርስ የዜና ወኪል አስረድተዋል።
ባለፉት ዘጠኝ ቀናት በተካሄደ የቁፋሮ ስራ የ115 ነዋሪዎች አስከሬን የተገኘ ሲሆን፣ በርካታ ከአደጋው የተረፉ ሰዎች አሁንም ድረስ የገቡበት አለመታወቁን ነዋሪዎች ይገልጻሉ።

ቁፋሮ የማካሄዱ ስራ የተጓተተ እንደሆነ ቅሬታቸውን ሲገልፁ የቆዩት ነዋሪዎች የከተማው አስተዳደርም ሆነ መንግስት ከአደጋው መገኘት ያልቻሉ ሰዎች ሙሉ ለሙሉ እስኪገኙ ድረስ ፍለጋው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
ከእንግዲህ በኋላ ከቁፋሮው በነፍስ የሚገኝ ሰው ይኖራል ብለን አናምንም የሚሉት ነዋሪዎች ተጨማሪ የቁፋሮ ቁሳቁስ እንዲሰማራ ተደርጎ አስከሬን የማፈላለጉ ስራው ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።
ከአንድ ሳምንት በፊት የቆሻሻ ክምሩ በመኖሪያ ቤቶች ላይ በተደረመሰ ጊዜ በትንሹ 48 ቤቶች ሙሉ ለሙሉ መውደማቸውንና በእያንዳንዱ መኖሪያ ቤት በአማካይ ሰባት ሰው ይኖር እንደነበር ገልጸዋል። ይሁንና የከተማው አስተዳደር የመኖሪያ ቤቶቹን መውደም ቢያረጋግጥም ምን ያህል ሰዎች በአካባቢው ይኖሩ እንደነበርና አስከሬናቸው ሊገኝ ያልቻለ ሰዎች ምን ያህል እንደሆነ የሰጠው ዝርዝር መረጃ የለም።
ከአንድ ሳምንት በኋላ በአካባቢው ቁፋሮ ቢቀጥልም በቂ የመሳሪያ ቁሳቁስ ባለመኖሩ የቆሻሻ ክምሩ በፍጥነት እየተነሳ አለመሆኑን ቅሬታ አቅራቢዎቹ ይገልጻሉ።
አቶ ጸጋዬ የተባሉ የረጲ ነዋሪ፣ አደጋው የደረሰባቸው ነዋሪዎች የቆሻሻ ክምሩ ለበሽታና ለተለያዩ ማህበራዊ ችግሮች እየዳረጋቸው እንደሚገኝ ከአንድ አመት በፊት ሲገልፁ መቆየታቸውንና የተወሰደ እርምጃ አለመኖሩን ለሮይተርስ አስረድተዋል።
የቆሻሻ መጣያ ቦታውን ከአንድ አመት በፊት ለመዝጋት ውሳኔ ተደርሶ የነበረ ሲሆን፣ የከተማ አስተዳደሩ አማራጭ ጠፍቷል በሚል በአካባቢው ቆሻሻ ማከማቸት መቀጠሉ ከአደጋው የተረፉት ነዋሪዎች ተናግረዋል።
አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማትና የተለያዩ አካላት ለአደጋው መድረስ መንግስትን ተጠያቂ ቢያደርጉትም፣ መንግስት በበኩሉ ነዋሪዎቹ በቆሻሻ ክምሩ ላይ ቁፋሮን በማካሄዳቸው ምክንያት አደጋው ሊደርስ መቻሉን መግለጹ ይታወሳል።

No comments:

Post a Comment