Monday, March 27, 2017

በምስራቅ አፍሪካ የተከሰተው የድርቅ አደጋ ወደ 700ሺ ህጻናትን ህይወት ሊያሳጣ እንደሚችል ተገለጸ


ኢሳት (መጋቢት 18 ፥ 2009)
ኢትዮጵያን ጨምሮ በሶስት የምስራቅ አፍሪካ ሃገራት እየተባባሰ ባለው የድርቅ አደጋ ወደ 700ሺ የሚጠጉ ህጻናት ህይወታቸውን ሊያጡ እንደሚችል ወርልድ ቪዥን የተሰኘ የእርዳታ ድርጅት ሰኞ አሳሰበ።
በደቡብ ሱዳንና ሶማሊያ የድርቁ አደጋ ወደ ረሃብ በመለወጡ ምክንያት ሰዎች በመሞት ላይ መሆናቸውን የገለጸው የሰብዓዊ ተቋሙ በኢትዮጵያና ኬንያ ድርቁ እየከፋ መምጣቱን በጉዳዩ ዙሪያ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በኢትዮጵያ የሶማሌ ክልል ድርቁ እየከፋ መምጣቱንና የእርዳታ አቅርቦት በበቂ ሁኔታ አለመኖሩን ችግሩን እንዳባባሰው ባለፈው ሳምንት መግለጹ ይታወሳል።

የካቶሊክ ዕርዳታ ድርጅት ተወካዮች በበኩላቸው በሶማሌ ክልል ከዚሁ የድርቅ አደጋ በተገናኘ የተበከለ የግድብ ውሃን የጠጡ ስድስት ሰዎች መሞታቸውንና ሌሎች በርካታ ሰዎች በጎዴ እና አጎራባች ባሉ ከተሞች በህክምና ላይ እንደሚገኙ ባለፈው ሳምንት ሪፖርት ማቅረባቸውም አይዘነጋም። “በአራቱ የምስራቅ አፍሪካ ሃገራት አፋጣኝ ርብርብ የማይደረግ ከሆነ በቀጠናው አሳዛኝ ክስተት ይታያል” ሲሉ በወርልድ ቪዥን የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት የምስራቅ አፍሪካ ተወካይ የሆኑት ክርስቶፈር ሆፍማን ገልጸዋል።
የሰብዓዊ ዕርዳታ ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በደቡብ ሱዳን፣ በሶማሊያና ኬንያ በድርቅ ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ እንደሆነም ሃላፊው አክለው አስታውቀዋል።
ከአምስት አመት በፊት በምስራቅ አፍሪካ በተለይ በሶማሊያ ተከስቶ በነበረው ተመሳሳይ የድርቅና የረሃብ አደጋ 260 ሺ የሆኑ አብዛኞቹ ህጻናት መሞታቸው የሚታወስ ነው።
በኦሮሚያ፣ አፋር፣ ሶማሌና የደቡብ ክልሎች ስር በሚገኙ በርካታ ዞኖች ተከስቶ ባለው አዲስ የድርቅ አደጋ 5.6 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ለአስቸኳይ የምግብ ድጋፍ ተጋልጠው እንደሚገኙ ይታወቃል።
ይሁንና፣ በሶማሌ ክልል ያለው ሁኔታ እየተባባሰ መምጣቱን ለሰው ህይወት ስጋት መሆኑን የተለያዩ የእርዳታ አካላት በመግለጽ ላይ ናቸው።
የክልሉ መንግስት በበኩሉ በአንድ ዞን ብቻ 40ሺ የቁም እንስሳት መሞታቸውና የምግብ እጥረቱ ለሰዎችና ለእንስሳት አስከፊ እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል።

No comments:

Post a Comment