Thursday, December 8, 2016

በቢሊዮን ብር የሚቆጠር ኪሳራ የደረሰበት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ባንክ ከፍተኛ ውዝግብ ውስጥ መግባቱ ተነገረ

ኢሳት (ኅዳር 29 ፥ 2009)
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ባንክ ለሃገር ውስጥና ለውጭ ባለሃብቶች መሬትን ለማቅረብ ሊያካሄድ ከነበረው ስራ ጋር በተገናኘ ያጋጠመው በቢሊዮን ብር የሚቆጠር ኪሳራ አዲስ ውዝግብ መቀስቀሱ ተግለጸ።
የፌዴራልና የክልል ባለስልጣናት ለደረሰው ኪሳራ ሃላፊነቱን ማን መውሰድ እንዳለበት ለአንድ አመት ያህል ምክክርን ሲያካሄዱ ቢቆዩም ጉዳዩ ዕልባት አለማግኘቱ ታውቋል።
በጋምቤላ ክልል ብቻ ከ100 የሚበልጡ የሃገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች ለኢንቨስትመንት የሚሆን ሰፊ የእርሻ መሬት ቢሰጣቸውም የፌዴድራል ባለስልጣናት የመሬት ርክክቡ ህገወጥ ነው በማለት ባለሃብቶቹ ስራቸውን እንዲያቆሙ መወሰኑ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በበኩሉ በዚሁ ክልል ተመሳሳይ ይዞታ ላይ በርካታ ባለሃብቶች በቢሊዮን ብር የሚቆጠር ብድር በመውሰድ ኪሳራ ማጋጠሙ በቅርቡ ይፋ አድርጓል።


በተመሳሳይ መሬት ላይ ብድርን ሲወስዱ የነበሩና ቁጥራቸው በትክክል ያልተገለጸ የህንድ ባለሃብቶች ብድራቸውን እንደያዙ ከሃገር የወጡ ሲሆን መንግስት የተዘረፈውን ገንዘብ ለማስመለስ የህግ ዕርምጃ በመውሰድ ላይ መሆኑን ይገልጻል።
ይኸው በጋምቤላ ክልል ለአምስት አመት ያህል ጊዜ ሲካሄድ የቆየ የመሬት ርክክብ ፕሮግራም በኢትዮጵያ ልማት ባንክ በቢሊዮን የሚቆጠር ኪሳራ ማድረሱ በተደጋጋሚ ሲገልፁ ቆይቷል።
የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት ከዚሁ ድርጊት ጋር ተያይዟል በተባለ እርምጃ የባንኩ ፕሬዚደንት የሆኑት አቶ ኢሳያስ ባህሬን ከሃላፊነት እንዲነሱ ያደረገ ሲሆን፣ በምትካቸው የብሄራዊ ባንክ ምክትል ገዢ የነበሩት አቶ ጌታነህ ናና ተሹመዋል።
ይሁንና ከሃላፊነታቸው የተነሱት አቶ ኢሳያስ ለስምንት አመት ያህል ጊዜ ካገለገሉበት ቦታ ለምን እንደተነሱ ግልፅ እንዳልሆነላቸው መግለጻቸውን አፍሪካ ቢዝነስ መጽሄት ዘግቧል።
በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት የተቋቋመ አንድ ቡድን በጋምቤላ ክልል የደረሰውን ኪሳራ እንዲያጣራ ቢቋቋምም ቡድኑ የምርመራ ግኝቱን በአንድ አመት ውስጥ ይፋ ሊያደርግ አለመቻሉ ታውቋል።
በመንግስት ላይ ድርሷል የተባለው በቢሊዮን ብር የሚቆጠር ኪሳራ በአሁኑ ወቅት ሃላፊነቱ በማን ላይ እንደሆነ ለህዝብ ለማሳወቅ በከፍተኛ ባለስልጣናት ዘንድ አለመግባባት መቀስቀሱን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አካላት አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የደረሰበትን ኪሳራ ተከትሎ መንግስት ለባለሃብቶች የሚሰጥ የኢንቨስትመንት መሬትና ብድር እንዲቆም ያደረገ ሲሆን፣ በአለም አቀፍ ደረጃ የመሬት ቅርምት ነው የተባለው ይኸው ዕርምጃ ከጥቅሙ ይልቅ ኪሳራው መብለጡን የተለያዩ አካላት ይገልጻሉ።

No comments:

Post a Comment