ኢሳት (ታህሳስ 5 ፥ 2009)
በኢትዮጵያ በተያዘው የፈረንጆች አመት ከቱሪዝም ገቢ 400 ሚሊዮን ዶላር (ወደ አንድ ቢሊዮን ብር) አካባቢ ልታጣ እንደምትችል ተገለጸ።
በሃገሪቱ ተግባራዊ ተደርጎ የሚገኘው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን አለመረጋጋት በቱሪዝም እንቅስቃሴው ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖን እያሳደረ እንደሚገኝ አፍሪካ ኒውስ መጽሄት የተለያዩ መረጃዎችን ዋቢ በማድረግ ረቡዕ ባቀረበው ዘገባ አስፍሯል።
በፈረጆች 2015 አም ኢትዮጵያ ከቱሪዝም ዘርፍ ወደ ሶስት ቢሊዮን ዶላር አካባቢን አግኝታ የነበረ ሲሆን፣ በ2016/2017 አም ተመሳሳይ ገቢን ለማግኘት እቅድ ተይዞ እንደነበር ለማግኘት እቅድ ተይዞ እንደነበር ታውቋል።
ይሁንና የተለያዩ ሃገራት ዜጎቻቸውን ወደ ኢትዮጵያ እንዳይጓዙ የጣሉትን እገዳ ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ ቱሪስቶች ቀድመው የያዙትን የጉዞ ፕሮግራም መሰረዛቸው ይፋ መደረጉ ይታወቃል።
የብሪታኒያ መንግስት ለዜጎቹ የሰጠውን የጉዞ ማሳሰቢያ ተከትሎ በሃገሪቱ የሚገኙ አስጎኚ ድርጅቶች ወደ ኢትዮጵያ የሚያደርጉትን ጉዞ የሰረዙ ሲሆን፣ ሌሎች የአውሮፓ ሃገራትም ተመሳሳይ ዕርምጃ መውሰዳቸው ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ቱሪዝም ኮሚሽን በኢትዮጵያ ያለው የአቸኳይ ጊዜ አዋጅ የውጭ ሃገር ቱሪስቶች እንቅስቃሴ እንደማይጎዳና አዋጁ ቱሪስቶችን የማይመለከት መሆኑን ቢገልፅም ጎብኚዎች ወደ ሃገሪቱ ከመጓዝ ተቆጥበዋል።
በዚሁ ድርጊት ኢትዮጵያ በፈረጆች 2016/2017 አም ወደ 400 ሚሊዮን ዶላር ልታጣ እንደምትችል አፍሪካ ኒውስ መጽሄት በጉዳዩ ዙሪያ ባቀረበው ዘገባ አስነብቧል።
የባህል ቱሪዝም ሚኒስቴር በበኩሉ ባለፉት ሶስት ወራት ብቻ ሃገሪቱ ከቱሪዝም ዘርፍ ከ7 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማጣቷን አረጋግጧል።
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስተር በተደጋጋሚ ለዜጎቹ የሰጠው የጉዞ ማሳሰቢያ ቀጥተኛ ተፅዕኖ ማሳደሩንም የተለያዩ አካላት ይገልጻሉ።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ገቢ ከሃገሪቱ አመታዊ አጠቃላይ ምርት 4.5 በመቶ የሚሆነውን በመሸፈን ለአንድ ሚሊዮን ሰዎች የስራ ዕድል መፍጠሩን የአለም ባንክ መረጃ ያመለክታል።
ይሁንና ዘፉ ካለፈው አመት ጀምሮ እየደረሰበት ያለው ተፅዕኖ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ጫናን እያሳደረ እንደሚገኝ ለመረዳት ተችሏል።
No comments:
Post a Comment