ኢሳት (ታህሳስ 5 ፥ 2009)
በኢትዮጵያ ሲካሄድ ከቆየው ህዝባዊ ተቃውሞ ጋር በተገናኘ መንግስት በጸጥታ ሃይሎች የተወሰዱ የሃይል ዕርምጃዎች ሽፋን እንዳያገኙ በትንሹ የ16 የመገናኛ ብዙሃንን ተቋም ድረገጾች እንዲዘጉ ማድረጉንም አምነስቲ ኢንተርናሽናል ረቡዕ አዲስ ባወጣው ሪፖርት አስታወቀ።
የማህበራዊ ድረ-ገጾችን ጨምሮ የኢንተርኔት አገልግሎት ሙሉ ለሙሉ ለመዝጋትና ለመቆጣጠር በተካሄደው በዚሁ የአፈና ዕርምጃ የተቃዋሚ ፓርቲ እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች አካላት ሰለባ መሆናቸውን የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ ኦፕን ኦብዘርባቶሪ ኦፍ ኔትዎርክ ኢንተርፊረንስ ከተሰኘ ተቋም ጋር በጋራ ያካሄደውን ጥናት አስመልክቶ ባወጣው ሪፖርት አመልክቷል።
ባለፈው አመት በተለይ በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ የኢንተርኔት አገልግሎትን ለመዝጋት የተወሰደው ዕርምጃ ተግባራዊ ተደርጎ በሚገኘው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅትም መቀጠሉን ሁለቱ አለም አቀፍ ተቋማት ገልጸዋል።
በስልጣን ላይ ያለው ገዢው የኢህአዴግ መንግስት ተግባራዊ አድርጎት የሚገኘው የቴክኖሎጂው የአፈና ድርጊት በሃገሪቱ ያለውን ግፍና ጭቆና በአግባቡ ለማወቅ እንዳላስቻለ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ባለስልጣናት ለመገናኛ ብዙሃን አስረድተዋል።
በመንግስት የተወሰደው ይኸው መጠነ ሰፊ ዕርምጃ የህግ መሰረት የሌለው መሆኑን በአምነስቲ ኢንተርናሽናል የአፍሪካ ቀንድና የምስራቅ እንዲሁም የታላላቅ ሃይቆች ምክትል ሃላፊ የሆኑት ሚቼል ካጋሪ ለአለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን አስረድተዋል።
በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ይወሰዱ የነበሩ የሃይል ዕርምጃዎች በበቂ ሁኔታ አለም አቀፍ ትኩረት እንዳያገኙ በትንሹ 16 የመገናኛ ብዙሃን ድረ-ገጾች የዘመቻውን ሰለባ መሆናቸውን ሃላፊው ገልጸዋል።
በሀገሪቱ ሁሉንም የሃሳብ ማንጸባረቂያ አማራጮችን ከመዝጋት ይልቅ ባለስልጣናት እየተነሱ ላሉ ህዝባዊ ጥያቄዎችና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ትኩረት መስጠት እንደሚገባቸው ሁለቱ አለም አቀፍ ተቋማት በሪፖርታቸው አሳስበዋል።
ለአንድ አመት ዘልቆ በቆየው የኦሮሚያ ክልል ህዝባዊ ተቃውሞ ከ700 የሚበልጡ ሰዎች በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች መገደላቸውንና ተመጣጣኝ ያልሆነ የሃይል ዕርምጃ ሲወስድ መቆየቱን አምነስቲ ኢንተርናሽናል ሲገልጽ ቆይቷል።
መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ አለም አቀፍ ተቋማትና የሃገራት ተወካዮች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራዊ መደረግን ተከትሎ መንግስት በኢንተርኔት አገልግሎት ላይ የወሰደው ዕርምጃ በዕለት ከዕለት ስራቸው ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩን በተደጋጋሚ ሲገልፅ እንደነበር ይታወሳል።
በጉዳዩ ዙሪያ ምላሽን የሰጡት የመንግስት ምክትል ቃል አቀባዩ አቶ መሃመድ ሰይድ የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጥ የለም ሲሉ ለአሶሼይትድ ፕሬስ ተናግረዋል።
በሁለቱ አለም አቀፍ ተቋማት ይፋ የተደረገውን ሪፖርት መሰረት የሌለው ነው ሲሉ የገለጹት ቃል አቀባዩ በሞባይል የኢንተርኔት አገልግሎት ላይ ከተከሰተ መጠነኛ መስተጓጎል በስተቀር የተወሰደ ዕርምጃ የለም ሲሉ አስተብብለዋል።
ይሁንንና ጠቅላይ ሚኒስስትር አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝን ጨምሮ የተለያዩ ባለስልጣናት የኢንተርኔት አገልግሎቱን ለማቋረጥ የተወሰደው ዕርምጃ በሃገሪቱ የተቀሰቀሰን ተቃውሞ ዕልባት ለመስጠት ነው ሲሉ ለህዝብ መግለጻቸው ይታወሳል።
No comments:
Post a Comment