Friday, August 18, 2017

በኦሮሚያ በቀጣዩ ሳምንት አጠቃላይ የስራ ማቆም አድማና ተቃውሞ መጠራቱ ታወቀ

(ኢሳት ዜና –ነሐሴ 12/2009)በኦሮሚያ በቀጣዩ ሳምንት አጠቃላይ የስራ ማቆም አድማና ተቃውሞ መጠራቱ ታወቀ። በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች የሚገኙ ወጣቶች በህቡዕ በመንቀሳቀስ በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች በሚቀጥለው ሳምንት ረቡእ ጀምሮ ለ5ቀናት የሚቆይ አድማ ለማድረግ ዝግጅት ላይ መሆናቸውን መረጃዎች ያሳያሉ። በሌላ በኩል በአማራ ክልል በተለይም ባህርዳርን ጨምሮ በምስራቅና ምዕራብ ጎጃም ሌላ ዙር አድማና የተቃውሞ እንቅስቃሴ ሊደረግ እንደሚችል እየተነገረ ነው። ለነሃሴ 10 ተራዝሞ በነበረው የግብር መክፈያ ቀነ ገደብ አብዛኛው የንግዱ ማህብረሰብ ባለመክፈሉ በአንዳንድ አካባቢዎች ውጥረት መንገሱን መረጃዎች ያመለክታሉ።
ሱቆች እየታሸጉ ነው። የነጋዴዎች እስርም ቀጥሏል። ከሚቀጥለው ረቡእ ጀምሮ ለ5 ቀናት የሚቆይ አድማ በመላው ኦሮሚያ የተጠራው የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ፣በሕዝቡ ላይ ያለአግባብ የተጫነውን ግብር በመቃወምና ከሶማሌ ክልል ጋር በተያያዘ በተነሳው የወሰን ግጭት የተገደሉትን ለማስታውስ ነው። ከዚህ ቀደም የነበሩ አድማዎች በውስን ቦታዎች የሚካሄዱና የተዘበራረቁ ነበሩ።በተለይም በአምቦ በወሊሶና በተወሰኑ የኦሮሚያ አካባቢዎች ከግብርና ከፖለቲካ እስረኞች ጋር በተያያዘ የተካሄዱ አድማዎች መጠነኛ ግጭቶች ከደረሱ በኋላ በአገዛዙ ታጣቂዎች የሃይል እርምጃ ለማፈን ሙከራ ሲካሄድባቸው የነበሩ ናቸው። አሁን ከመጪው ረቡእ ጀምሮ በኦሮሚያ ቄሮዎች ወይም ወጣት ስብስቦች የተጠራው አድማ ግን ለ5 ቀናት በኦሮሚያ እንደሚካሄድ ያወጡት መግለጫ ያመለክታል። በዚሁም ሁሉም የንግድ መደብሮች ተሽከርካሪዎችና የሕዝብ ማመላለሻዎች ከስራ ውጭ እንደሚሆኑ ጥሪ ቀርቧል። የኦሮሚያ ወጣቶች የጠሩት አድማ ዶክተር መረራ ጉዲና፣አቶ በቀለ ገርባና ሌሎች የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ አመራር አባላት ከእስር እንዲፈቱ የሚጠይቅ ነው ተብሏል። በኦሮሚያና ሶማሌ ክልል አዋሳኝ አምስት አካባቢዎች በድንበር ይገባኛል ጥያቄ ሰበብ በሕወሃት አገዛዝ ጣልቃገብነት የሚካሄዱ ግጭቶችም ወጣቶቹን እንዳሳሰባቸው ወጣቶቹ ገልጸዋል። እናም በሶማሌ ልዩ ሃይል አባላት የተገደሉ የኦሮሚያ ነዋሪዎችን ለማሰብ ይህ አድማ መጠራቱን ቄሮዎቹ አስታውቀዋል። አድማውን የጠሩት የኦሮሚያ ወጣቶች ክልሉ ይህን የተቃውሞ እንቅስቃሴ ለማደናቀፍ በሚሞክሩ ማናቸውም ሃይሎች ላይ እርምጃ እንደሚወስዱም አስጠንቅቀዋል። በአድማው ወቅት ተሽከርካሪዎቻቸውን የሚያንቀሳቅሱ ሁሉ ለሚገጥማቸው ችግር ሐላፊነቱን እንደሚወስዱም ነው ያሳሰቡት። ይህ በእንዲህ እንዳለም በአማራ ክልል ከግብር ጋር በተያያዘ ያለው ተቃውሞ ከፍተኛ ውጥረት እየፈጠረ መሆኑ ታውቋል። በአማራ ክልል የግብር መክፈያው ጊዜ ነሐሴ 1/2009 ከተጠናቀቀ በኋላ ግማሾቹ የንግድ መደብሮቻቸውን በመዝጋት ሲጠፉ ሌሎቹ ደግሞ ሳትከፍሉ ቆይታችኋል በሚል ነጋዴዎችን እያንገላቷቸው መሆኑ ታውቋል። በባህር ዳር ያልተጠበቀ ፍተሻና የሰራዊት ከበባ እንደነበርም ተገልጿል።



No comments:

Post a Comment