Tuesday, October 28, 2014

ህወሃትና የጦር አበጋዞቹ እሴቶች

ህወሃት የትግሬ ተወካይ ብቻ ሳልሆን ለትግራይ ህዝብ የሚያመልከውን አምላክም ጭምር የምመርጥለት እኔ ነኝ በሚል እብሪት ውስጥ ይገኛል። በዚህ እብሪቱም እየተመራ የምታመልኩትን ልመርጥላችሁ ብሎ አጠቃላይ ሙስሊሙንም ክርስትያኑንም እያመሰው እንደሆነ እያየን ነው። እኔን የማይቀበል እጣ ፈንታው ከመታመስ በላይ የሆነ ወዮታ ነው የሚል ያልተፃፈ አዋጅም አለው። ህወሃት በትግራይ ትከሻ ላይ ተፈናጦ፤ ትግራይን ምርጫ አሳጥቶ እኔን እምኑ መንገዳችሁም ህይወታችሁም እኔ ብቻ ነኝ ብሎ ራሱን የትግራይ ጣዖት አድርጎ ሹሟል። ይሄን ጣዖት አንቀበልም፤ እኛ የራሳችን ሂሊና ያለን እንደ ሰው ማሰብ የምንችል ነን ያሉ ብዙ የኢትዮጵያ ልጆች ባልታወጀው አዋጅ መሠረት አብዮታዊ ፀሎት እየተፀለየላቸው አፈር ለብሰው ቀርተዋል።የህወሃት የእብሪቱ መጀመሪያ “እኔ ያልኩት ካልሆነ ሁሉም ገደል ይግባ” ማለቱ ነው። የትግራይ ተወካይ እኔ ብቻ ነኝ ሌላው ሁሉ የትግራይ ህዝብ ጠላት ነው የሚል እምነቱ የድርጅቱን ሥር የሰደደ መሠሪነትና እብሪት የሚያሳይ ነው።

ብዙ ኢትዮጵያዊያን ህወሃት የቆመው ለትግራይ ህዝብ ነው የሚል ዕምነት አሳድረዋል። ይሄን አስተሳሰብ መቀበል የሚጠቅመው ለህወሃት ብቻ ነው።ህወሃት ለትግራይ ህዝብ ክብርም ፍቅርም ያለው ቡድን አይደለም። ለትግራይ ህዝብ በጎ ምኞት እና ክብር ያለው ቢሆን ኑሮ የትግራይ ህዝብ የወደደውን እንዲመርጥ፤ ያልወደደውን እንዲተው ያልተሸራረፈ ነፃነት እንዲኖረው ያደርግ ነበር። እኛ እንደምናየው ግን የትግራይ ህዝብ የወደደውን ለመምረጥ፤የጠላውን ለመተው እንዲችል ነፃነትያለው ህዝብ አይደለም። የትግራይ ህዝብ ነፃነቱን በነፃነት ሥም ያጣ ህዝብ ሁኗል። ህወሃቶች የትግራይን ህዝብ ነፃነት ሸራርፈው ሸራርፈው ህዝቡን በሙሉ መያዣ አድርገውና ከወገኑ ለይተውት እየገዙት ይገኛሉ። የትግራይም ህዝብ ሳይወድ በግዱ ህወሃቶችን ተሸክሞ መከራው በዝቶ እየተገዛ ይገኛል።

ህወሃት መራሽ በሆነው መከላከያ ድህረ-ገፅ ላይ “ያልተሸራረፈ ዲሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ማስረፅ” እሴታችን ነው የሚል መፈክር በጉልህ ተፅፏል። ህወሃቶች መከላከያ ኃይሉ የቆመው የህዝቡን ያልተሸራረፈ ዲሞክራሲዊያ አስተሳሰብ ለመንከባከብ ነው እያሉን ነው። የህዝቡ ዲሞክራሲያዊ መብት ሳይሸራረፍ ተከብሮ ቢሆን ኑሮ ጋዜጠኛ ሚሊዮን ሹርቤ ተሰዶ ሂዶ በባዕድ አገር ባልሞተ ነበር። ህዝቡ በኑሮ ውድነት ባልተሰቃየ ነበር፤ አገሪቷ ሠላም ርቋት እዚህም እዚያም የዜጎች ደም በከንቱ ባልፈሰሰ ነበር፤ የአገሪቷ ብሄራዊ አንድነት ላልቶ ዜጎች ይሄ ክልል አገራችሁ አይደለም እየተባሉ ከኖሩበት መንደር ውጡ ባልተባሉ ነበር፤ ዜጎቿ አገር ውስጥ ከመኖር ይልቅ በባህር ውስጥ አዞ መበላትን ምርጫቸው ባላደረጉ ነበር። አገሪቷ እንዲህ ምስቅልቅሏ ወጥቶ ባለበት ሁኔታ ህወሃቶች ያልተሸራረፈ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብን መንከባከብ የሚችል ሠራዊት ገንብተናል እያሉ እያላዘኑ ይገኛሉ። ይሄንንም ለማጠናከር ስንል የጦር አበጋዞችን መሾም አስፈልጎናል ብለው የአንደኛ ደረጃ ፊደል ቆጥረው ያልዘለቁ ሽፍቶችን ሹመት በሹት እያደረጓቸው ነው።

“ዘላለማዊ ክብር” በሰይጣን መንፈስ ሲመራ ለነበረው ለመለስ ዜናዊ ይገባል ብሎ የሚያመነው “ክርስትያኑ” ደሳለኝ ኃ/ማሪያም በመለስ ዜናዊ መንፈስ እየተመራ ስልጣኑን ከያዘ ግዜ ጀምሮ 4 ሌተናል ጄኔራሎች፤ 9 ሜጄር ጄኔራሎች፤ 28 ብርጋዴር ጄኔራሎችን ሹሟል። ብዙ ሰዎች ግን ደሳለኝ ኃ/ማሪያም በዚህ ሹመት ውስጥ የመወሰን ድምፅ የለውም ይላሉ። እንዲያውም ደሳለኝ የነብሩን ጭራ ይዞ እንዳይለቀው ጭንቅ ሆኖበት የሚኖር ብኩን ግለሰብ ነው ሲሉም ያክላሉ። ያም ሆነ ይህ ደሳለኝ ኃ/ማሪያም የመለስ ዜናዊን ራዕይ ሊያስፈፅም በትር ስልጣኑን ጨብጧልና በእርሱ ዘመን ለሚሆነው ሁሉ ኃላፊነት ይወስዳል።

ወደ ጦር አበጋዞቹ እንመለስ ከእነዚህ የጦር አበጋዞች መካከል አብዛኞቹ የህወሃት አባሎች መሆናቸው የታወቀ ነው። በዚህ ጥቅምት ወር ብቻ 3 ሌተናል ጄኔራሎች እና 3 ሜጄር ጄኔራሎች ተሹመዋል። እነዚህ የጦር አበጋዞች በየትኛው መደበኛ ጦር አውድማ ላይ ውለው ለዚህ ማዕረግ የሚያበቃቸውን ምግባር እንደፈፀሙ የሚያውቅ የለም። ሽፍቶች እና ጎሬላ ተዋጊዎች መሆናቸው ግን የሚካድ አይደለም። የሽፍትነትና የጎሬላ ውጊያ ልምድ ግን ለዚህ ማዕረግ የሚያበቃቸው ሊሆን እንደማይችል የታወቀ ነው።

ሌተናል ጄኔራል ሁነው ከተሾሙት መካከል

1ኛ. አብርሃም ወ/ማሪያም

2ኛ. አደም መሃመድ

3ኛ. ብርሃኑ ጁላ

ሲሆኑ ወደ ሜጀር ጄኔራልነት ያደጉት ደግሞ

1ኛ. ክንፈ ዳኘ

2ኛ. ተክለብርሃን ወ/አርጋይ

3ኛ. ዘውዱ እሸቴ ይባላሉ።

የእነዚህ የጦር አበጋዞች ሹመት ባላቸው የትምህርት ደረጃ፤ ለህዝባቸው ባላቸው ክብር፤ ለአገራቸው ባላቸው ፍቅር ሳይሆን ለጣዖቱ ህወሃት ያላቸው ታማኝነት ሚዛን ደፍቶ በመገኘቱ ነው።

ከስድስቱ የጦር አበጋዞች መካከል የአራቱ ሹመት ቤተሰባዊ ዝምድናን መሠረት ያደረገ ስለመሆኑ የሚከተለውን ትሥሥር እንድትመለከቱ እንጋብዛላእን።

1ኛ. በሌተናል ጄኔራልነት ማዕረግ የተሾመው አብርሃም ወ/ማሪያም የመለስ ዜናዊ የሥጋ ዘመድ ነው። የመለስ ዜናዊ ቅደመ አያት በጎን ከሌላ ሴት የወለዷቸው ሴት ልጅ ልጅ ነው።

2ኛ. ሜጄር ጄኔራል ክንፈ ዳኜ ደግሞ አባቱ አቶ ዳኜ ገ/ስላሴና የመለስ አባት የአቶ ዜናዊ እናቶች እህትማማቾች ናቸው።

3ኛ. ሜጄር ጄኔራል ዘውዱ እሸቴ ደግሞ የመለስ ዜናዊን የቅርብ ዘመድ አግብቶ በጋብቻ ተሳስሯል። ሚስቱ ደግሞ በ18 ዓመት ታንሰዋለች።

4ኛ. ሜጀር ጄኔራል ተክለብርሃን ወ/አረጋይ የመለስ ዜናዊ የአክስት ልጅ ነው።

ይህ መከላከያ ኃይል ተብሎ የአንድን ጎጠኛ ድርጅት ህልውና ለመጠበቅ የቆመውን ቡድን የሚመሩት የጦር አበጋዞች በትምህርት ደረጃቸው ከሚያዟቸው ተራ ወታደሮች የማይሻሉ፤ ከራሳቸው ወዲያ ህዝብና አገር የሚባል ነገር የማያውቁ፤ በአገኙት አጋጣሚ ሁሉ የአገሪቷን ሃብት ለመዝረፍ የሚሸቀዳደሙ እና ራሳቸውን እንደ ኢንቨሰተር የሚቆጥሩ፤ የውትድርናን ሙያ ከነፍስ ግዲያና ከጭካኔ ለይተው የማያዩ እና ርህራሄ የሌላቸው ስለመሆናቸው የህወሃት ድርሳናት ይመሰክራሉ።

ህወሃት ርህራሄን የማያውቁ ጭካኞችን የጀግንነት ማዕረግ እየሰጠ በአገሪቷ ላይ እያሰማራ ይገኛል። የህወሃቶች ስነ-ምግባርም ሆነ ስነ-ልቦና ለጀግንነት የሚያበቃቸው አይደለም። በህወሃት መንደር ጀግናና ጀግንነት አይታወቁም። ጀግና እውነትን አይፈራም። ህወሃት እውነትን ስለሚፈራ ገና ድክ ድክ የሚሉ ነፃ ሚዲያዎችን ያለ ምንም ማወላወል ሊደመስሱ የሚሸቀዳደሙትን ይሾማል። ጀግና ነፃ ሚዲያን የሚፈራበት ምንም ምክንያት አይኖረውም። ጀግና ነፍሰ ገዳይ አይደለም። ህወሃት ህፃን ነብዩን የመሰሉ እንቦቀቅላዎችን ግንባር ግንባራቸውን ብለው ለመግደል የማይራሩ ጨካኞችን ይሾማል። ጀግና ሌብነትን ከልቡ ይፀየፋል። ህወሃት ግን ሌብነትን የሚፀየፉትን ሳይሆን የድሃ ንብረት ሰርቆ ሃብት ማካበትን እንደ ብልጠት የሚቆጥሩ ደካሞችን ጄኔራል እያለ ያሰማራል።

በዚህ በጥቅምት ወር የተሾሙት 6 የጦር አበጋዞች ለሹመት ሲታጩ የትምህርት ዝግጅታቸውና ብቃታቸው፤ ለአገራቸው ያደረጉት የላቀ አስተዋፅዖ፤በውጊያ አውድማ ያሳዩት ጀግንነት ታይቶ ነው የሚል ወሬ ከህወሃት መንደር ተሰምቷል። ህወሃቶች እና ደጋፊዎቻቸው ይሄን ለማመን አይቸገሩም። የእነዚህ ቡድኖች ዋና መለያ የገዛ ውሸታቸውን እውነት ነው ብለው አምነው ጥሩ እንቅልፍ መተኛት የሚችሉ መሆናቸው ነው። የገዛ ውሸቱን እውነት ነው ብሎ የሚያምን ግለሰብ ብርቱ የሆነ የስነ-ልቦና ቀውስ ውስጥ የወደቀ መሆንኑ የስነ-አዕምሮ ተማራማሪዎች ይናገራሉ። ህወሃቶችም ብርቱ በሆነ የስነ-ልቦና ቀውስ ውስጥ እንደሚገኙ ለማየት የዕለት ተዕለት ውሸቶቻቸውን እና የሚፈፀሙትን ፀያፍ ድርጊቶች ማየት በቂ ይሆናል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል በጥቂት በዘረ ሃረጋቸውና በቤተሰብ ክር በተሳሰሩ ወንበዴዎች እጅ ወድቋል። በእነዚህ ዘራፊዎች የሚመራ የሠራዊት ኃይል የህዝቡን ዲሞክራሲያዊ መብት ማስከበር አይቻለውም። የጦር አበጋዞቹ የአገሪቷን አንጡራ ሃብት እየዘረፉ ከገነቧቸው ህንፃዎች በየወሩ የሚሰበስቡትን ገንዘብ የሚጠይቅ ለህዝብ ወገንተኛ የሆነ መንግስት እንዲመሰረት ምንም ፍላጎት አይኖራቸውም። ለእነዚህ ጦር አበጋዞች ነፃነት፤ ፍትህ፤ እኩልነት እና እውነተኛ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚባሉ ነገሮች ያሸብሯቸዋል። እነዚህንም ጥያቄዎች ያነሳ አሸባሪ ተብሎ የዚህን ምድር ሥቃይ እንዲያይ ይደረጋል።ይሄ ቡድን ሥልጣን ላይ እስከቆየ ድረስ ነፃነት ፤የህግ የበላይነት፤ እኩልነት የሚባሉ እሴቶች በኢትዮጵያ ይሰፍናሉ ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው።

በመጨረሻም ተራው ወታደር እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ነፃነቱን ተገፎ ለምንና ለማን እንደሚገልና እንደሚሞት ሳያውቅ በገዛ ወገኖቹ ላይ እየተኮሰና የንፁህ ደም እያፈሰሰ እንደሚኖር እያየን ነው። ተራው ወታደር ጋምቤላ ሂዶ ያገኘውን ሁሉ የሚገድለው ለምንድ ነው? ኦጋዴን ሂዶ የዘር ማጥፋት ወንጀል የሚፈፅመው ለምንድ ነው? ጉራፋርዳ ወርዶ የመዥንግሮችን ደም የሚያፈሰው በምን ምክንያት ነው? ያልተሸራረፈ ዲሞክራሲን አስፍነናል ከተባለ ይሄ ሁሉ ውጊያ ምንጩ ምንድ ነው? ሠራዊቱ ለእነዚህና ለመሰል ጥያቄዎች በቂ መልስ መፈለግ ይኖርበታል።ምንም ትርጉም በሌለው ውጊያ ውስጥ እየሄደ የንፁህ ደም ማፍሰሱን ለማቆምና ነገ በወንጀል ከመጠየቅ ራስንም ለማዳን ሠራዊቱ ራሱን ከዘረኞቹና ከዘራፊዎቹ የጦር አበጋዞች መለየት ይኖርበታል።ከእርሱ በሞራልም ሆነ በትምህርት ደርጃቸው ከማይሻሉ ጄኔራል ተብየዎች ራሱን ለይቶ ለነፃነት፤ ለፍትህ እና ለእኩልነት ከሚታገሉ ኃይሎች ጎን እንዲሰለፍ ጥሪያችንን አሁንም እናስተላልፋለን።

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !


No comments:

Post a Comment