Sunday, May 25, 2014
ከአያት መገናኛ የተነጠፈው የባቡር ሐዲድ እየተቀየረ ነው
በአዲስ አበባ ቀላል የከተማ ባቡር መስመር ዝርጋታ ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ በሚገኘው የአያት መገናኛ መስመር ላይ የተነጠፈው ሐዲድ፣ ከመሥፈርቱ ውጪ በመሆኑ ምክንያት በሌላ ሐዲድ በመቀየር ላይ ነው፡፡
ከሳምንት በፊት የተጀመረው ቀደም ሲል የተዘረጋውን ሐዲድ የመቀየር ሥራ በአሁኑ ወቅት ከአያት ወደ ሲኤምሲ አካባቢ መድረሱን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ጉዳዩን በተመለከተ የፕሮጀክቱ ኮንትራክተር የሆነውን ቻይና ሬልዌይ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽንና የፕሮጀክቱ ተቆጣጣሪ የሆነውን ስዌድሮድ የተባለ የስዊድን ኩባንያ ሪፖርተር ለማነጋገር ቢሞክርም፣ በኮንትራት ስምምነቱ መሠረት ለሚዲያ መግለጫ መስጠት እንደማይችሉ ገልጸዋል፡፡
ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ግን የፕሮጀክቱ ኮንትራክተር የመጀመሪያውን ሐዲድ የማንጠፍ ሥራ ሲጀምር፣ በኮንትራት ስምምነቱ ላይ በተቀመጡት መሥፈርቶች መሠረት እንዲሠራ ተነግሮት ነበር ብለዋል::
በኮንትራት ስምምነቱ ላይ የተቀመጠው መሥፈርት አንዱ ባለ 25 ሜትር ሐዲድ ከሌላኛው ጋር የሚገናኘው በኦክስጅን ብየዳ እንደሆነ ቢገልጽም፣ ኮንትራክተሩ ግን የተቀመጠውን መሥፈርት እያወቀና በተቆጣጣሪ (አማካሪ) ድርጅቱ በተደጋጋሚ እየተነገረው ሐዲዱን መዘርጋት እንደቀጠለበት ምንጮች አስረድተዋል፡፡
አማካሪ ድርጅቱ ባለበት ኃላፊነት መሠረት ጉዳዩን ከማሳሰብ ባለፈ ለተዘረጋው ሐዲድ የሚቀርብ የክፍያ ጥያቄን እንደማያጸድቅ ግልጽ በማድረጉና በሌሎችም ምክንያቶች፣ ኮንትራክተሩ የስምምነት መሥፈርቱን ለማክበር እንደተገደደ ያስረዳሉ፡፡
ከአያት መገናኛ ባለው መስመር ላይ ተነጥፈው የነበሩት ሐዲዶች ብዛት 960 ሲሆኑ፣ እያንዳንዳቸው 25 ሜትር ርዝመት እንዳላቸው የሚያስረዱት ምንጮች፣ እየተነሱ ያሉት በመሥፈርቱ መሠረት መበየድ የማይችሉ ሆነው ስለተገኙ እንደሆነ ገምተዋል፡፡
‹‹ሙሉ በሙሉ መቀየር አለባቸው፡፡ ይህ ማለት ግን አገልግሎት አይሰጡም ማለት አይደለም፡፡ ምናልባት ከአዲስ አበባ ጂቡቲ ለሚዘረጋው የባቡር መስመር ሊያገለግሉ ይችላሉ፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡
አሁን ለተፈጠረው ችግር ምክንያቱ ኮንትራክተሩ እንደሆነ፣ ወጪውም ሙሉ በሙሉ የራሱ እንደሚሆን የሚያስረዱት ምንጮች፣ በዚህ ምክንያት የፕሮጀክቱ ጊዜ ተስተጓጉሏል ማለት እንደማይቻል ይገልጻሉ፡፡
የሚሰጡት ምክንያት ደግሞ ሐዲድ ማንጠፍ በዚህ ፕሮጀክት ላይ ቀላሉ የሥራ ዓይነት መሆኑን፣ በአጠቃላይ 34 ኪሎ ሜትሩ ላይ ሐዲድ የማንጠፍ ሥራ በአንድ ወር ማጠናቀቅ የሚቻል መሆኑን ይገልጻሉ፡፡
ጉዳዩን በተመለከተ የአዲስ አበባ ቀላል የከተማ ባቡር ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር በኃይሉ ስንታየሁ ተጠይቀው፣ የተነጠፈውን የሐዲድ መስመር የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ አፅድቆ እንዳልተረከበ ተናግረዋል፡፡
የኮንትራት ስምምነቱ የሐዲድ መስመሩ ‹‹ኮንቲኒየስሊ ዌልድድ›› ወይም አንድ የሐዲድ ብረት ከሌላኛው ጋር ያለምንም ክፍተት ተበይዶ መያያዝ እንዳለበት ያመለክታል ብለዋል፡፡ በመገናኛ አያት መስመር ላይ የተዘረጋው በዚህ መሠረት ሳይሆን ብሎን በማያያዝ በመሆኑና ይህ ደግሞ መሥፈርቱን የማያሟላ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ሪፖርተር በሥፍራው ተዘዋውሮ እንደተመለከተውና በፎቶግራፉ ላይም እንደሚታየው ቀደም ሲል የተነጠፉት ሐዲዶች እየተነሱ ነበሩ፡፡
የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር በኃይሉ ግን፣ ‹‹እየተነሱ ያሉትን በማሳሰብና በማጠጋጋት ለመበየድ ነው እንጂ የሐዲድ ብረቶቹ እየተቀየሩ አይደሉም፤›› በማለት ያስተባብላሉ፡፡
የሐዲድ ማንጠፍ ሥራው ከመጀመሪያውኑ በመሥፈርቱ መሠረት ለምን በብየዳ አልተሠራም በማለት ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ ‹‹መጀመሪያና መጨረሻ የሚባል ነገር በአሁኑ ወቅት የለም፡፡ እኛ ገና አልተረከብናቸውም፡፡ ምክንያቱም ገና ሒደት ላይ ነው ብለዋል፤›› ብለዋል፡፡
ቀደም ሲል የተነጠፉትን ሐዲዶች በሌላ የመቀየር፣ እርስ በርስ የመበየድና የማያያዝ ተግባር በጐተራ መስመር ላይም መጀመሩን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በዚህ ላይም የተጠየቁት ኢንጂነር በኃይሉ፣ የተነጠፉት ሐዲዶች እርስ በርስ ባልተበየዱባቸው ወይም በብሎን ብቻ በተያያዙባቸው ቦታዎች ላይ ሁሉ የመበየዱ ሥራ እንደሚከናወን ገልጸዋል፡፡
ethiopianreporter/news
የአዲስ አበባ ቀላል የከተማ ባቡር ፕሮጀክት 34 ኪሎ ሜትር ሲሸፍን፣ ከምሥራቅ ምዕራብ እንዲሁም ከሰሜን ደቡብ የሚዘረጋ ነው፡፡ አጠቃላይ የፕሮጀክቱ ወጪ 475 ሚሊዮን ዶላር እንደሚሆን ሲጠበቅ፣ ከጠቅላላ ወጪው 85 በመቶ የተገኘው ከቻይና መንግሥት በብድር ነው፡፡
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment