(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 30/2011) በኢትዮጵያ በአንዳንድ የሃገሪቱ ክልሎች ያለውን የጸጥታ ችግር ለመፍታት በመከላከያ ሰራዊት የሚመራ ኮማንድ ፖስት በመቋቋም ላይ መሆኑን የመከላከያ ሚኒስትሯ ገለጹ።
የሃገር መከላከያ ሚኒስትሯ ኢንጂነር አይሻ መሃመድ ለፓርላማው ዛሬ እንደገለጹት በክልሎች ጥያቄ ጸጥታ ወደ ደፈረሰባቸው አካባቢዎች የገባው የመከላከያ ሰራዊት የህዝቡን ደህንነት ለማስጠበቅ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል።
ባለፉት 6 ወራት ከ7ሺህ በላይ የሰራዊት አባላት መሰናበታቸውንም ገልጸዋል።
ቦታዎቹ ወይንም ክልሎቹ የትኞቹ እንደሆኑ የመከላከያ ሚኒስትሯ ባይገልጹም በኦሮሚያና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ድንበር እንዲሁም በጉጂ ዞን የመከላከያ ሰራዊት መሰማራቱ ታውቋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር/ኦነግ/ ጋር የጀመረው ውዝግብ መፍትሄ ሳያገኝ በቀጠለበት በአሁኑ ወቅት የመከላከያ ሰራዊት የጸጥታ ችግር ወዳለባቸው አካባቢዎች እንዲሰማራ መደረጉ መንግስት የኦነግን እንቅስቃሴ በሃይል ለማስቆም መወሰኑን ያሳያል ተብሏል።
የሃይማኖት አባቶችና የሃገር ሽማግሌዎች ችግሩን በሰላም ለመቋጨት በርካታ ጥረቶች ማድረጋቸውም ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከመምህራን ጋር ባለፈው ሳምንት ባደረጉት ውይይት የኦነግን እንቅስቃሴ ለወራት በትዕግስት ሲያዩት መቆየታቸውን መግለጻቸው ይታወሳል።
20 እና 30 ዓመታት ምንም ፍሬ በማያፈራ ሁኔታ ውስጥ ካለበት በክብር ያመጣናቸው በኤርትራና በሶማሊያ ያደረጉት የነበረውን ጦርነት ወለጋ ውስጥ እንዲያመጡት አይደለም ማለታቸው አይዘነጋም።
በሌላም በኩል የሃገር መከላከያ ሚኒስትሯ ዛሬ በፓርላማ ባቀረቡት ሪፖርት ባለፉት 6 ወራት 7 ሺህ 17 የሰራዊቱ አባላት መሰናበታቸውን ገልጸዋል።
ተሰናባቾቹም በዕድሜ የማዕረግ ዕድገት ፈተናን ባለማለፍ እንዲሁም በትምህርት ደረጃቸው ዝቅተኛነት የተሰናበቱ መሆናቸውን አመልክተዋል።
No comments:
Post a Comment