Tuesday, September 12, 2017

በኢትዮጵያ የዋጋ ግሽበቱ ወደ ሁለት አሀዝ አድጎ በሐገሪቱ የኢኮኖሚ መናጋት እየፈጠረ መሆኑን የምጣኔ ሐብት ባለሙያዎች ገለጹ

(ኢሳት ዜና–መስከረም 2/2010) በኢትዮጵያ የዋጋ ግሽበቱ ወደ ሁለት አሀዝ አድጎ በሐገሪቱ የኢኮኖሚ መናጋት እየፈጠረ መሆኑን የምጣኔ ሐብት ባለሙያዎች ገለጹ። የማእከላዊ ስታስቲክስ ማእከል በበኩሉ በተለይ ከፍተኛ የእህል ዋጋ ግሽበት በመኖሩ የኢኮኖሚ ቀውስ መከሰቱን ገልጿል። በኢትዮጵያ ያለው አገዛዝ የዋጋ ግሽበቱን ከ8 በመቶ በታች አደርገዋለሁ እያለ ሲዝት ቢቆይም በአሁኑ ጊዜ በከፍተኛ መጠን ጨምሮ 10 ነጥብ 4 በመቶ መድረሱ ታውቋል። በኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ የተመዘገበው የዋጋ ግሽበት ባለፉት 22 ወራት ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ነው። የግሽበቱ መንስኤ ደግሞ ከእህል ምርት ማነስና የምግብ ሸቀጦች ዋጋ በመጨመሩ ነው ተብሏል። የፎርቹን አዲስ ጋዜጣ ዘገባ እንደሚያመለክተው ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ የታየባቸው እህሎች ጤፍ፣በቆሎ፣ገብስ፣ስንዴና የመሳሰሉት ናቸው። የማእከላዊ ስታስቲክስ ዋና ዳይሬክተር አቶ ቢረሳው ይገዙ
እንደገለጹትም በኢትዮጵያ በተለይ በጥራጥሬ እህሎች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ እየታየ ነው። እናም የምግብ እህል የዋጋ ግሽበቱ ብቻ በ13 ነጥብ 3 በመቶ ባለፈው ወር ብቻ ተመዝግቧል ነው ያሉት። ይህም ባለፈው አመት ከነበረው ሁኔታ ጋር ሲነጻጸር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። የዋጋ ግሽበቱ ደግሞ በዘንድሮው አመት ከፍተኛ የኢኮኖሚ እድገት ይመዘገባል እያለ ከሚዝተው መንግስት ጋር ተቃራኒ መሆኑን የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ይናገራሉ። በአዲስ አበባ እህል ገበያ የጅምላ አከፋፋይ የሆኑት ዳቢ ንጉሴ ከእህል ዋጋ ጋር በተያያዘ የጤፍና የበቆሎ ዋጋ በእጅጉ ማሻቀቡን ይናገራሉ።የበቆሎ ዋጋ ብቻ በኩንታል 3 ሺ ብር እየተሸጠ መሆኑን በመግለጽ። የጤፍ ዋጋ ደግሞ ከዚህ የባሰና የናረ ዋጋ ላይ መሆኑን ጅምላ ነጋዴው አስታውቀዋል። የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች እንደሚሉት ለእህሎች ዋጋ መናር ዋነኛው ምክንያት በሀገሪቱ የተከሰተው ድርቅ ነው። ዘንድሮ በኢትዮጵያ የተከሰተው የተምች ወረርሽኝም ለችግሩ ማባባስ ሌላኛው ምክንያት መሆኑን ታዛቢዎች ይናገራሉ። በተምች ሳቢያ እህላቸው የወደመባቸው አርሶ አደሮችም በአደባባይ ሲያለቅሱ እንደነበር ዘገባዎች አመልክተዋል።

No comments:

Post a Comment