ፌስቡክ ላይ በጻፋቸው ፅሁፎች ምክንያት የሽብር ክስ ቀርቦበት ጉዳዩ በፍ/ቤት እየታየ የሚገኘውና በእስር ቂሊንጦ ያለው የቀድሞው የሰማያዊ ፓርቲ ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ በሚገኝበት እስር ቤት ውስጥ ከአርብ ህዳር 2/2009 ዓ.ም ጀምሮ ቀንና ሌሊት በሰንሰለት ታስሮ እንደሚገኝ ታውቋል፡፡
አቶ ዮናታን ተስፋዬ ለዚህ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የዳረገው ህዳር 2/2009 ዓ.ም የፍርድ ቤት ቀጠሮ የነበራቸው እነ አቶ በቀለ ገርባ ወደ ፍርድ ቤት አንሄድም በሚል ከቂሊንጦ እስር ቤት አስተዳደር ጋር አለመግባባት ፈጥረው ድብደባ ሲደርስባቸው አቶ ዮናታን ‹‹ለምን ትደበድቧቸዋላችሁ፤ በመግባባት ቢሆን አይሻልም ወይ›› በሚል ለግልግል ጣልቃ መግባቱን ተከትሎ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል፡፡
አቶ ዮናታን ተስፋዬ በተለይ አብሮት የታሰረው አቶ አዲሱ ቡላላ ላይ ድብደባ ሲደርስበት ‹‹ተው አትደባደቡ›› በማለቱ ‹‹ምን አገባህ›› ተብሎ በራሱም ላይ ከፍተኛ ድብደባ ተፈጽሞበት ከዚያ ወዲህ በሰንሰለት ለመታሰር እንደተዳረገ ታውቋል፡፡
አቶ ዮናታን ተስፋየ ሰንሰለቱ የሚፈታለት ቤተሰቦቹ ሊጎበኙት ሲጠራ ብቻ እንደሆነም የመረጃው ምንጮች ያስረዳሉ፡፡ አቶ ዮናታን መከላከያ ማስረጃዎችን ለማድመጥ ለህዳር 19/2009 ዓ.ም ተለዋጭ የፍ/ቤት ቀጠሮ ላይ እንደሚገኝ ይታወሳል፡፡
No comments:
Post a Comment